ለምርምር ወደ ፈረንሳይ የተወሰዱ ከ800 በላይ ቅሪተ አካላት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
ለምርምር ወደ ፈረንሳይ የተወሰዱ ከ800 በላይ ቅሪተ አካላት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ ፈረንሳይ ለሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ከኢትዮጵያ በውሰት ወስዳቸው የቆዩ ከ800 በላይ የሚሆኑ ቅሪተ አካላትን ለኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስረከበች።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መንግስታት መልካም ፈቃድ ለጥናትና ምርምር ወደ ፈረንሳይ ተወስደው የነበሩ ከ800 በላይ የአርኪኦሎጂና የፓሊዮንቶሎጂ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው በመመለሳቸው ዛሬ የርክክብ መርሃ ግብር አካሂዷል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በዚሁ ወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ቢታወቅም በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ አካባቢ የአርኪኦሎጂና የፓሊዮንቶሎጂ ቅሪተ አካላት የሚጠኑበት ላብራቶሪ አልነበረም።
በዚህ ወቅት የፈረንሳይ አርኪኦሎጂና ፓሊዮንቶሎጂ ጥናት ተቋማት ፋና ወጊ በመሆን ትብብር አድርገዋል ብለዋል።
በሁለቱ አገራት መንግሥታት ትብብር ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ በታችኛው አዋሽ ሸለቆና በመልካ ቁንጡሬ አካባቢ የተሰበሰቡ ቅርሶች ለምርምር ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ ብሔራዊ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም መወሰዳቸውን አስታውሰዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች የተደረጉ ጥናቶች የጉማሬ፣ የአውራሪስ፣ የዝሆን፣ የሜዳ አህያና የመሳሰሉ ታላላቅ አጥቢዎች ዝግመተ ለውጥ ያሳዩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ይህም ታችኛው ኦሞ እና አዋሽ ሸለቆዎች ዓለም አቀፍ ቅርሶች እንዲሆኑና ኢትዮጵያ በሥነ-ሕይወት ዝግመተ ለውጥና በሰው ዘር መገኛነቷ ቀዳሚ ስፍራ እንድትይዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
አሁንም የፈረንሳይ አርኪኦሎጂና ፓሊዮንቶሎጂ ጥናት ተቋም እና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጠንካራ ቁርኝት ያላቸው ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የቅሪተ-አካል ምርምር አቅም በእጅጉ መጎልበቱንና ጥቂት ቀደምት ቅሪተ-አካላት ካልሆኑ በስተቀር ሁሉንም በሀገር ውስጥ መመርመር የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል።
የቀሩትንም ጥቂት ቅሪተ-አካላት በሀገር ውስጥ ለመመርመር የሲቲ ስካን አገልግሎት ካላቸው ሆስፒታሎች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም አክለዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ጁሌን ቮይቱሬዝ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ተመራማሪዎች የሰው ልጅ አመጣጥ ግንዛቤያችንን ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮችን ለበርካታ አስርት ዓመታት በታችኛው ኦሞና አዋሽ ሸለቆዎች ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
የጥናቱ ግኝቶች ለዓለም አቀፍ የፓሊዮ-አንትሮፖሎጂ ታሪክ ልዩ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል።
ይህ የማስረከብ ሂደት ቅርስ በተገኘበት ሀገር ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ እና እሴት እንዲሰጠው ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ቅርሶቹን መጠበቅም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።