የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የዲጂታል አገልግሎትን በማጠናከር የግብር አሰባሰቡን ይበልጥ ውጤታማ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የዲጂታል አገልግሎትን በማጠናከር የግብር አሰባሰቡን ይበልጥ ውጤታማ እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን በማጠናከር የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ይበልጥ ውጤታማ በማድረግና የግብር ከፋዮችን እንግልት የሚያስቀሩ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የከተማዋን የግብር አሰባሰብ ሂደት በማዘመን፣ ፍትሃዊ፣ ፈጣንና ከብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ ለማከናወን ተግባራዊ በተደረጉ አዳዲስ አሰራሮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ በዚሁ ውቅት እንዳሉት፤ ተቋሙ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመዲናዋ ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ሂደትን ለማስፈን፣ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የማዘመን፣ ብቁ የሰው ሃይል የማፍራት እንዲሁም የተገልጋዮችን እርካታ የማሳደግ ተግባራትን በስፋት አከናውኗል።
በዚህም ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች ወርሃዊ የቫት (VAT) እና የሰራተኞች ደሞዝ ግብር ማስታወቂያን በአካል ወደ ቅርንጫፍ መሄድ ሳይጠበቅባቸው በኦንላይን ማሳወቅ የሚያስችላቸውን አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል።
ይህ አሰራር ለገቢ አሰባሰቡ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በላይ ግብር ከፋዮች ጊዜያቸው እና ገንዘባቸው ሳይባክን አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።
በ2019 ዓ.ም ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ግብራቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው በኦንላይን አማካኝነት የሂሳብ መዝገቦቻቸውን በማሳወቅ ክፍያ የሚፈጽሙበት ዘመናዊ አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል።
ቢሮው አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ከማዘመን ጎን ለጎን፣ የ2018 ዓ.ም የግብር ዘመን የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች የዴስክ ኦዲት ስራዎችን በጥራት ለመስራት እና በሂደቱ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችል "የዴስክ ኦዲት ማስፈጸሚያ ሰነድ" ማዘጋጀቱን አብራርተዋል።
ይህ ሰነድ መዘጋጀቱ የሂሳብ መዝገብ የሚይዙ የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች ከዚህ ቀደም ለኦዲት ስራ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ከማሟላት አንጻር የሚታዩ ችግሮችን የሚቀርፍ ነው ብለዋል።
በግብር ሰብሳቢውና በከፋዩ መካከል የሚስተዋሉ አለመግባባቶችንም ለመቅረፍ ከፍተኛ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
በተለይም ሰነዱ ከባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴ እና ከእቁብ ገንዘብ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ያስችላል።
ከንግድ እንቅስቃሴ ውጭ በብድር፣ በውርስ፣ በስጦታና በመሳሰሉት የተገኙ ገንዘቦች እንደ ንግድ ትርፍ ተቆጥረው ግብር እንዳይጣልባቸው ሊቀርቡ የሚገባቸውን ማስረጃዎች በግልጽ ያመላክታል ብለዋል።
ግብር ከፋዮች ለቢዝነስና ለቁጠባ ዓላማ የሚያውሏቸውን የባንክ አካውንቶችን ለይተው እንዲያስቀምጡ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የዴስክ ኦዲት ማስፈጸሚያ ሰነዱ የግብር ከፋየች የሂሳብ መዝገቦች ውድቅ ሊደረጉባቸው የሚችሉ መንስኤዎችን በግልጽ እንደሚዘረዝርም አክለዋል።
የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ያለቅጣት አሳውቀው ክፍያ የሚፈጽሙበት ጊዜ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ብቻ በመሆኑ፣ ግብር ከፋዮች የተሟላ የሂሳብ መዝገቦቻቸውንና መግለጫዎቻቸውን ቢሮው በዘረጋው የኦንላይን አሰራር በመላክ የዜግነት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።