ቀጥታ፡

የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነትና የአመራርነት ሚና ማሳደግ ዘላቂ ልማትና  ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው

ድሬዳዋ ፣ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፡-የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነትና የአመራርነት ሚና ማሳደግ ዘላቂ ልማትና  ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተመለከተ።

የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴት አመራሮች የተሳተፉበትና ለሴት ምሁራን  የአመራርነት ሚና መጎልበት አስቻይ ምህዳር ለመፍጠር የሚያግዝ  የምክክር ጉባኤ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል።


 

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ኡባህ አደም (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት  የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነትና የአመራርነት ሚና ማሳደግ  ዘላቂ ልማትና  ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

በዚህ ረገድ መንግስት በየደረጃው ባሉ የአመራርና ሌሎች እርከኖች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ለሀገር እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንኑ ተከትሎም በዘርፉ የሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በአግባቡ እንዲፈጸሙ ለማስቻል ሀሳቦች የሚንሸራሸሩባቸውን መድረኮች ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት ማከናወን እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዚህ እረገድ  በዘርፉ ጅምር ስራዎችን ለማላቅና ለውጤት ለማብቃት መሰል መድረኮች ወሳኝ አበርክቶ አላቸው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቷ አክለውም ሴቶች በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአመራር ሰጪነት፣ በመማር ማስተማርና በምርምር ስራዎች ተሳትፎ በሚያደርጉበት፣ የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን በሚሳድጉበትና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሴት ተማሪዎች ተሞክሮ ልውውጥ በሚደረጉባቸው ጉዳዮች ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

 አምባሳደር ገነት ዘውዴ( ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣት የተጀመረውን ጥረት ማገዝ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ሴቶች በሁሉም መስክ ተሳትፏቸውን ለማሳደግና ከውጤት ለመብቃት በራስ መተማመን መንፈስ መትጋት እንዳለባቸው ተሞክሯቸውን መሰረት በማድረግ ምክራቸውን የለገሱት ደግሞ በኢንዱስትሪና ንግድ ዘርፍ አርአያና ውጤታማ የሆኑት ወይዘሮ ሀድያ መሀመድ ናቸው።

 መድረኩ ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም