በሰመራ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኘን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰመራ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኘን ነው
ሠመራ፤ጥቅምት 18/2019(ኢዜአ):- በሰመራ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ጊዜና ወጪን የቆጠበ አገልገሎት እያገኙ መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ።
ማእከሉ በሚሰጠው ፈጣን አገልግሎት የተገልጋዮች እርካታ እየጨመረ መምጣቱ ተመላክቷል።
በማዕከሉ አገልግሎቱን ካገኙት መካከል አቶ መሐመድ ሳልህ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም የተለያዩ ቢሮዎች በመሄድ ለእንግልትና ለአላስፈላጊ ወጪ ይዳረጉ ነበር።
አሁን ላይ በማእከሉ የተለያዩ አገልገሎቶች በአንድ ቦታ በመሰጠታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የንግድ ፈቃድ ስያሜ አውጥተው ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በማእከሉ ባገኙት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ጊዜና ወጪያቸውን መቆጠብ እንደቻሉ አስታውቀዋል።
ሌላዋ ተገልጋይ ቃልኪዳን አማረ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች አሁን ላይ በማእከሉ በአንድ ቦታ ላይ እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም አገልግሎቶቹ በዲጂታል የታገዙ በመሆናቸው ውክልና የመስጠት ጉዳያቸውን ያለውጣ ውረድ በአጭር ጊዜ ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በማእከሉ የመጡበትን የውልና ማስረጃ ጉዳይ ባጠረ ጊዜ ማጠናቀቃቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ሲራጅ አህመድና አቶ ኑር ሁሴን አደም ናቸው ።
ከዚህ ቀደም በተራራቀ ቦታ ይሰጡ የነበሩ አገልገሎቶችን በማእከሉ በአንድ ቦታ ማግኘት መቻላቸውን የገለጹት ተገልጋዮቹ በማእከሉ ባገኙት ፈጣንና ቀልጣፋ መስተንግዶ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የሰመራ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ከሊል ዓሊ በበኩላቸው እንዳሉት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህብረተሰቡ ጉዳይ ለማስፈጸም ይደርስበት የነበረውን አላስፈላጊ እንግልትና ወጪ ማስቀረቱን ተናግረዋል ።
በዚህም ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት እንዲጨምር ማድረጉንም አመልክተዋል።
በማእከሉ እየተሰጠ ባለው ፈጣን አገልግሎት የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው በማእከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን የማስፋት ስራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል ።