አፍሪካ በአንድ ድምጽ ልትናገር፣ በራሷ አቅምም ልትለማ ይገባል!! - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ በአንድ ድምጽ ልትናገር፣ በራሷ አቅምም ልትለማ ይገባል!!
በእንግዳው ከፍያለው ከባህርዳር ኢዜአ
12ኛው የጣና ፎረም በባሕር ዳር ከተማ ሞቅ ደመቅ ብሎ ተካሂዶ በተሟላ ስኬት ተጠናቋል፣ አፍሪካውያን በራሳቸው እውቀት፣ የአመራር ጥበብና አቅም ችግሮቻቸውን ተወያይተውና ተመካክረው ለመፍታት የታተሩበት ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ፣ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበርና የቡሩንዲ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊክ ሀዳዲ፣ የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኪቱሬ ኪንዲኪ እና የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የቀድሞ መሪዎች፣ ምሁራንና ወጣቶች በፎረሙ ታድመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፎረሙ መክፈቻ ላይ "እንኳን ወደ ሰው ልጅ መገኛና የዓባይ ወንዝ ምንጭ ወደ ሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ በደህና መጣችሁ" በማለት ለ12ኛው የጣና ፎረም ታዳሚዎች የመክፈቻ ንግግር አርገዋል።
የአፍሪካ መሪዎች አህጉሪቱ ጠንካራና ተደማጭ ድምጽ በዓለም አደባባይ እንዲኖራት ተባብረው መሥራት አለባቸው ሲሉ ባስተላለፉት መልእክት ። "ለአገራችን ኢትዮጵያም ዘላቂ ሰላምና ልማት ዋነኛ ጉዳያችን ነው። ሲቪሎችንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መጠበቅ ግዴታችን አድርገን እየሠራን እንገኛለን" ብለዋል።
"ለዚህም ችግሮችን በውይይትና በንግግር ለመፍታት የሚያስችል አገራዊ ምክክር አካሂደናል። በምክክሩ የተደረሱ ድምዳሜዎች ለፓርላማ ቀርበዋል፤ ወደ ታች በማውረድም መፍትሔ ለማምጣት በእንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን።"
"ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በመገንባት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን በማቅረብ ቀጠናውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ያስቻለ ውጤት አስገኝተናል። ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት ሰጥተን በመሥራታችን ባለፈው ዓመት ብቻ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ከወርቅ ሽያጭ አግኝተናል። ጥሬ ማዕድንን ከመላክ ይልቅ እሴት ለመጨመር የሚያስችል የወርቅ ማጣሪያ ማዕከል ገንብተናል። ይህም ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም አብሮ በመሥራት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ነው።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በፋይዳ ላይ የሠራነው ሥራ አበረታች ውጤት አስገኝቷል። የቀጣዩን የቴክኖሎጂ ትውልድ እውን ለማድረግ እየገነባን ያለነው 'የመደመር ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ' ከኢትዮጵያ አልፎ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ለአፍሪካ ዕድገትና ብልጽግና ትልቅ አቅም የሚሆን ነው።"
"የአፍሪካን ነጻ የንግድ ልውውጥ በማጠናከር፣ የገንዘብ ዝርፊያንና ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የአፍሪካ ኅብረትንና ቀጠናዊ ድርጅቶችን ማጠናከር ላይ መሥራት ይገባል። ድርጅቶቹ በራስ የገንዘብ አቅም እንዲተዳደሩ በማድረግ የፖሊሲ ነጻነትን ማረጋገጥ ይገባል። ኢትዮጵያ የኮፕ (COP) 32 ስብሰባን እንድታዘጋጅ ተመርጣለች፤ የአፍሪካ አገራትም ስብሰባውን በጋራ ተባብረው እንዲያዘጋጁ'' በማለት ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ያላትን የአብሮነት ስሜት አጋርተዋል።
ሌላው በጣና ፎረም መልዕክት ያስተላለፉት የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ እንደገለጹት፣ በአፍሪካ የሚስተዋለው የጸጥታ መደፍረስ፣ ሕገ ወጥ የመሣሪያና የሰዎች ዝውውር፣ የአማጽያን መስፋፋትና የመንግሥታት ወታደሮች አቅም መዳከም ከፊት ለፊት የሚታይ ችግር ቢሆንም፣ ዋናው የችግሩ ምንጭ ኢኮኖሚ ነው ብለዋል።
በጦርነቶች ወቅት የውጭ ኃይሎች በገንዘብም ሆነ በመሣሪያ ድጋፍ ጣልቃ በመግባት የአፍሪካ አገራት ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅምና እውቀት እንዳይፈቱ እንቅፋት ሆነዋል። በዚህም ሱዳንን ለሁለት የከፈለ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክን እያተራመሰ ያለ፣ ሶማሊያን የአሸባሪ መነሻ ያደረገ የሰላም መታጣት ችግር አጋጥሟል። የሞዛምቢክና የሳህል በረሃ አካባቢ አገራትም የችግሩ ሰለባ ናቸው። ይህ የሚያሳየው ግጭት በአፍሪካ እየተስፋፋ የመጣ እንጂ እየቀነሰ አለመሆኑን ነው።
የዘመኑን ግጭት የከፋ የሚያደርገው ርካሽና አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች በአማጽያኑ እጅ በመግባታቸው የአህጉሪቱን ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያወሳሰበው ይገኛል። ይህም ሲቪሎችን ለአደጋ የዳረገ ነው። የጣና ፎረምም ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች በነጻነት በመምከርና የመፍትሔ ሐሳብ በማፍለቅ ለአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማበጀት መፍትሔ አመንጪ አህጉራዊ ተቋም ሆኗል።
በቀጣይም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ፣ በተባበሩት መንግሥታት አፍሪካ የሚገባትን ቦታ ማግኘት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ፣ የውጭ ዕርዳታን ማስቆምና የራስን ወጪ በራስ አቅም በመሸፈን ዕድገትና ብልጽግናን ማረጋገጥ ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚገባ ሐሳብ አቅርበዋል።
ጆን ድራማኒ ማሃማ አያይዘውም፣ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካን ንቅናቄ ቀድማ በመቀላቀል አሻራዋን በማስቀመጧ አድናቆት ሊቸራት ይገባል ብለዋል። "አፍሪካ በአንድ ድምጽ በመናገር መብትና ጥቅሟን ልታስከብር ይገባል" ያሉት ደግሞ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የቡሩንዲ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ናቸው። የአፍሪካ አገራት ድንበራቸውን በመክፈት በጋራ መገበያየትና የንግድ ልውውጥ ማድረግ አለባቸው። ቡሩንዲና ታንዛኒያ በድንበር አካባቢዎች ባሉ ገበያዎች ይገበያያሉ፤ ይህም ዘላቂ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
"ያለ እርቅና ምክክር ሰላም አይረጋገጥም" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ "የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጦርነት ለመፍታት መሞከር ከንቱ ድካም ነው" ብለዋል። የአፍሪካን ችግር ስናስብ እንደታመመ የአንድ ሰው የሰውነት ክፍል አድርገን ማየት ይኖርብናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በናይል ተፋሰስ ኢትዮጵያና እኛ ተሳስረናል ብለዋል። ይህም ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ኢቦላ ያሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመግታት በጋራ መነጋገርና መሥራት ይገባል፤ ለዚህም የጣና ፎረም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ሌላዋ በፎረሙ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊክ ሀዳዲ፣ የአፍሪካ አገራት ድንበሮች የግጭት ሳይሆን የጋራ ብልጽግናና የትብብር በሮች መሆን አለባቸው ብለዋል። ለዚህም የአፍሪካ አገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት በመዘርጋት ለግጭቶች ፈጣን ምላሽ በመስጠት የአገር አንድነትንና የሕዝብ ደኅንነትን ማስጠበቅ አለባቸው ብለዋል።
"የኢኮኖሚ ነጻነትን በማረጋገጥ በራስ አቅም የመልማትና የማደግ ሕልምን እውን ማድረግ ይገባል" ያሉት አምባሳደር ሰልማ፣ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ትብብርና ዓለም አቀፋዊ አጋርነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። ፖሊሲዎቻችን ዘላቂ የሚሆኑት ሴቶችና ወጣቶችን የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል። አፍሪካውያን የራሳችንን መሠረተ ልማት በራሳችን አቅምና በጀት በመገንባት በቀጣናዊ እሴት ትስስር ማጠናከርና ክህሎት መፍጠር ይገባል ብለዋል። የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አህጉር በመፍጠር የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።
ከፎረሙ የአገራት መሪዎች ያስተላለፉት መልእክት አፍሪካን ከጦርነትና ግጭት ለማውጣት መሻት፣ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ማበልጸግ፣ ድንበሮች ተከፍተው ነጻ የንግድ ልውውጥ ማስፈን፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት ማረጋገጥና የተዋሐደች አህጉር ሆና ለማየት ያላቸውን ፍላጎትና ጉጉት ያሳያል። የፎረሙ ውይይት ማጠቃለያዎችም የመሪዎቹን ሐሳብ የሚያንጸባርቁ ነበሩ።