ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የውስጥ አቅምንና ግልጽ የልማት አቅጣጫን በመከተል እያስመዘገበች ያለው ለውጥ ተምሳሌት የሚሆን ነው 

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የውስጥ አቅምንና ግልጽ የልማት አቅጣጫን በመከተል እያስመዘገበች ያለው ለውጥ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት መሆኑ ተገለጸ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በተባበሩት መንግስታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ (UNFPA) በተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚሰሩ አፍሪካውያን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ የውስጥ አቅምንና ግልጽ የልማት አቅጣጫን በመከተል እያስመዘገበች ያለው ለውጥ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ነው።

በተባበሩት መንግሥታት የሥነ-ሕዝብ ፈንድ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ዚምባብዌያዊቷ ሊዲያ ዚጎሞ፤ በኢትዮጵያ እየታዩ ባሉ ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴዎች መደነቃቸውን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ተስፋን የሚሰንቅ የልማት እንቅስቃሴ ማየታቸውን ጠቅሰው፣ "የኢትዮጵያ መንግሥት የያዘው ግልጽ የዕድገት ራዕይ አስደንቆኛል" ብለዋል።

እነዚህ በሀገሪቱ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ወጣቶችን ጨምሮ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠሩና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጓቸው እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ይህም ለመላው አፍሪካ ተምሳሌት እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።


 

በተባበሩት መንግሥታት የሥነ-ሕዝብ ሕዝብ ፈንድ (UNFPA) የኢትዮጵያ ተወካይ ኮትዲቯራዊው ኮፊ ኩዋሜ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው የመጎብኘት ዕድል እንዳገኙ ጠቅሰው፣ እየታየ ባለው ልማት መደነቃቸውን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ልማት እንደሚታይ፣ በተለይም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ለዕድገት ወሳኝ የሆኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በትኩረትና በፍጥነት እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮፊ ኩዋሜ አክለውም፣ በሀገሪቱ ያለው ወጥ የልማት ራዕይ ዕድገቱ በፍጥነትና ሳይቋረጥ እንዲቀጥል እያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የሚያስገርም እንደሆነና ዕድገቱ የበለጠ ተስፈንጥሮ እንዲሄድ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም