ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ታንዛኒያ በካፒታል ገበያ ዘርፍ ተቋማዊ ትብብራቸውን ለማጎልበት ቁርጠኞች ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ታንዛኒያ በካፒታል ገበያ ዘርፍ ተቋማዊ የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ትብብራቸውን ለማጎልበት ቁርጠኞች መሆናቸውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክቶሬት የታላላቅ ሐይቆች ሀገራት ዳይሬክተር ተረፈ ቡርቃ ገለጹ።

ከዛሬ ጥቅምት 18 እስከ 20 ቀን 2019 ዓ.ም የሚቆየው የኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤቶች የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክቶሬት የታላላቅ ሐይቆች ሀገራት ዳይሬክተር ተረፈ ቡርቃ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ታንዛኒያ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።

የሀገራቱ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነትም በፓን-አፍሪካኒዝም እሴቶች ላይ የተመሰረተና የረጅም ዘመናት ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ተቋማቱ መድረክም የሀገራቱን ታሪካዊ ወዳጅነት በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትንና ትብብርን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።

መድረኩም የካፒታል ገበያ ልምድና ተሞክሮን በመጋራት ስትራቴጂካዊ የአሰራር ሥርዓትን መዘርጋት የሚያስችል የትብብር ምኅዳርን ለመገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የታንዛኒያ ካፒታል ገበያዎች ፍርድ ቤት ልዑካንም የመዲናዋን የእንግዳ ተቀባይነት ባህልና የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንደሚጎበኙ አንስተዋል።


 

 

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አብነት ዘርፉ በበኩላቸው፤ ካፒታል ገበያ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

የካፒታል ገበያም ከስኬታማ ሕጎችና ደንቦች ባሻገር በኢንቨስተሮች ጥበቃ፣ በሕዝብ እምነት፣ ተጠያቂነትና ውጤታማ የክርክር አፈታት ስልቶች ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያና የታንዛኒያ የካፒታል ገበያ የልምድ ልውውጥ መድረክም ውጤታማ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ዘመናዊ የሕግና የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ታንዛኒያ በአህጉራዊ ተቋማት ምስረታ ጠንካራ የትብብር ታሪክ ያላቸው ሀገራት ናቸው ያሉት ደግሞ የታንዛኒያ ካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ንቴሚ ኒሚልዋ ኪሌካማጀንጋ (ዶ/ር) ናቸው።


 

የሀገራቱ የካፒታል ገበያ የልምድና ተሞክሮ የትብብር መድረክም ጠንካራ የፋይናንስ ፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም