የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አዳዲስ እውቀቶች እና የትብብር አቅጣጫዎችን ለመለየት ትልቅ እድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አዳዲስ እውቀቶች እና የትብብር አቅጣጫዎችን ለመለየት ትልቅ እድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ የዘንድሮው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አዳዲስ እውቀቶችን ለመቅሰም፣ ልምድ ለመለዋወጥ እና ለቀጣይ የዘርፉ ዘላቂ ልማት የሚያግዙ የትብብር አቅጣጫዎችን ለመለየት ትልቅ እድል መፍጠሩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የ3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት "ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ ሳይንሳዊ መሠረት ያላቸውን ፖሊሲዎችና አጋርነቶችን ማሳደግ" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች መካሄዱን ቀጥሏል።
በዕለቱም በውሃ ሀብት አያያዝና ዘላቂ አጠቃቀም ዙሪያ ያተኮሩ የፓናል ውይይቶች፣ የኤግዚቢሽን ማሳያዎችና ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።
የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት ልማት ከፍተኛ ባለሙያ ዮሴፍ አበበ እንዳሉት፣ መድረኩ የውሃ ሀብትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመከታተል፣ የከርሰ ምድር ውሃን በጥናት የመለየት እና የቆሸሸ ውሃን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓቶችና የክትትል መሣሪያዎች የውሃ ሀብት ሁኔታን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት፣ የሚከሰቱ ለውጦችን በወቅቱ ለመለየት እና በጥናት የተደገፈ ውሳኔ ለመድረስ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የከርሰ ምድር ውሃን በጥናት መለየት እና በዘላቂነት መጠቀም እንደሚገባ አስረድተዋል።
በዉሀ እና ኢነርጂ ሚንስቴር የከተማ መጠጥ ውሃ ጥናት፣ ዲዛይን ግንባታ ክትትል ዴስክ ኃላፊ እና የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል አዜብ ታደሰ በበኩላቸው፤ መድረኩ በውሃ፣ በንጽህና እና በኢነርጂ ዘርፍ የተገኙ ሳይንሳዊ ጥናቶችን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮዎች ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥ የተገኙ ተሞክሮዎችን ከዓለም አቀፍ ልምዶች ጋር በማገናኘት፣ በመጠጥ ውሃና ንጽህና አገልግሎት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አዳዲስ እውቀቶችን ለመቅሰም እና ለቀጣይ የዘርፉ ልማት የሚያግዙ የትብብር አቅጣጫዎችን ለመለየት እያስቻለ የሚገኝ አስፈላጊ መድረክ መሆኑ አስገንዝበዋል።