ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት እና በአረንጓዴ ዐሻራ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች አርአያ የሚሆኑ ናቸው- ፋኦ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት እና በአረንጓዴ ዐሻራ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና በተሞክሮነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ረዳት ዋና ዳይሬክተር እና የአፍሪካ ተወካይ አበበ ኃይለገብርኤል(ዶ/ር)  ገለጹ።

የአፍሪካ ሳይንስና ኢኖቬሽን ፎረም 2026 በአዲስ አበባ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው።

ፎረሙ ሳይንስን፣ ቴክኖሎጂንና ኢኖቬሽንን በመጠቀም በአፍሪካ የምግብና ግብርና ሥርዓት ውስጥ ያሉ ተደራራቢ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የተዘጋጀ አህጉራዊ መድረክ ነው።

በተጨማሪም ፎረሙ ምርታማነትን በመጨመር፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ እና የግልና የመንግሥት ኢንቨስትመንቶችን በማሳደግ አህጉራዊ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ረዳት ዋና ዳይሬክተር እና የአፍሪካ ተወካይ አበበ ኃይለገብርኤል (ዶ/ር) ምርታማነትን ለማሳደግ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚመረተው ምርት ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፤ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም መንግሥታት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

በአፍሪካ ከፍተኛ የምርት ብክነት መኖሩን ገልጸው፤ የምርት ብክነትን ለመቀነስ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ራስን ለመቻል እያከናወነችው ያለው ሥራ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ተፈጥሮን በመንከባከብ በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በነዚህ ሥራዎቿ በሮም በተካሄደው የዓለም የምግብ ፎረም ላይ ዕውቅና ማግኘቷን አስታውሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም