ቀጥታ፡

የጉባ ብስራት አካል የሆነውን የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቤት ልማት ፕሮጀክት ማሳካት የሚያስችል አቅም ተገንብቷል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦የጉባ ብስራት አካል የሆነውን የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቤት ልማት ፕሮጀክት በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ጠንካራ አቅም መገንባቱን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 04 ቀን 2017 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅን ይፋ ካደረጉ በኋላ፣ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት በ30 ቢሊዮን ዶላር የሚገነቡ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን አብስረዋል።

የጉባ ብስራቶች ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ስብራት በማውጣት ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ናቸው።

የጉባ ብስራቶች የኒውክሊየር ማመንጫ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያ እና የቤቶች ልማትን ያካተተ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተሞች ልማትና በመኖሪያ ቤት ግንባታ ያከናወናቸው ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው።

በተለይም በቤት ልማት ዙሪያ ተግባራዊ የተደረጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና የአሠራር ሥርዓቶች የጉባ ብስራት አካል የሆነው የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቤት ልማት ፕሮጀክት ትልቅ ልምድ የተወሰደባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ በፋይናንስ፣ በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ እና ሌሎች መሰል ሰፋፊ የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በዘርፉ ያሉ አቅሞችን ወደ ተግባር በመቀየር የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት የማሟላት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አክለውም የመደመር መንግሥት የዜጎችን የቤት አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት ተግባራዊ ካደረጋቸው ውጤታማ ሥራዎች መካከል ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ የተከናወኑ ተግባራት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ለዚህም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድጉ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቅሰው፣ ይህም መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያመላክት ነው ብለዋል።

የተፈጠረው አስቻይ ሁኔታ ዘርፉ ሳቢ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን፣ በተደመረ አቅም ፕሮጀክቱ ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ እድል መፍጠሩን አንስተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም