የክልሉ ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ቦንጋ ፣ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተሞችን ለኑሮ ምቹ፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረኩን በቦንጋ ከተማ አካሄዷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ በወቅቱ እንደገለጹት፣ ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ለንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከተሞች የፖለቲካ፣ የኢንዱስትሪ፣ የአስተዳደር፣ የመሠረተ ልማት እንዲሁም የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዋና ማዕከላት በመሆናቸው፣ በየደረጃው የማዘመን ሥራ ላይ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠ አንስተዋል።
የመደመር መንግሥት ለከተሞች የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ በክልሉ ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙት የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተሞችን ገጽታ እየቀየሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይሁንና ፕሮጀክቶች የየአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበና ሙሉ ፓኬጁን ባሟላ መልኩ ከመሥራት አንጻር የሚስተዋለውን ውስንነት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራም አቶ በላይ ገልጸዋል።
በክልሉ ከተሞች የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ፕላንና ዘመናዊነትን ጠብቀው እንዲመሩ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
በከተሞች የሚገኘውን የመሬትና የኢንቨስትመንት ሀብት በአግባቡ በመለየት የሀብት ምንጭ ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት ኃላፊው፣ ዘመናዊ አሠራርን በመዘርጋት የሕዝቡን የአገልግሎት እርካታ ከፍ ለማድረግ በቅንጅት እንደሚሠራም አመልክተዋል።
መድረኩ በበጀት ዓመቱ በጥንካሬ የተመዘገቡ አፈጻጸሞችን በማስቀጠል መሻሻል የሚገባቸው ላይ በመምከር ውጤታማ ለመሆን በማለም መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ያለፉት ሦስት ወራት 66 ነጥብ 95 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታና ጠረጋ፣ እንዲሁም የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ 18 ነጥብ 66 ኪሎ ሜትር የመንገድ መብራትና የውኃ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን የገለጹት ደግሞ በቢሮው የልማትና በጀት ዕቅድ ዳይሬክተር አቶ ኬሮ አበበ ናቸው።
በዚህም 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት መግባቱን፣ እንዲሁም 5 ነጥብ 95 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መውረጃ ቦይ መገንባቱንም ተናግረዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል አስተያየት የሰጡት የሸካ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አንዷለም ጌታቸው እና የታርጫ ከተማ ከንቲባ አቶ ጌታሁን ደራ፣ መሬትን በዘመናዊ መልኩ የመምራትና የማስተዳደር ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን አሟጦ የመሰብሰብና የማኅበረሰቡን ተሳትፎ የማሳደግ ተግባራትን በማጠናከር ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የቢሮውና የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።