ቀጥታ፡

በምሥራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ጥበቃን ለማጠናከር አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ በምሥራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ጥበቃን ለማጠናከር አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

በምሥራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች፣ አጀንዳዎች፣ ተጋላጭነቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ላይ ያተኮረ ቀጣናዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስት የአፍሪኮ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) እየተካሄደ ይገኛል።
 

ሁለተኛ ቀኑን የያዘው ይህ ቀጣናዊ ጉባኤ "የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መቅረጽ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚደረግ ነው።

ስብሰባው የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (EAC) አባል ሀገራትንና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ያካተተ ሲሆን፣ በጊዜው እየተለዋወጠ የመጣውን የሰብዓዊ መብቶች ምህዳር በዘላቂነት መፍትሄ ለማስቀመጠና ተግባራዊ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ያለመ ነው።

በስብሰባው ላይ የሚነሱ ምክረ ሀሳቦች ከአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ ከአጀንዳ 2063 እና ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የሕዝቦችን ተሳትፎ ከሚያረጋግጡ አህጉራዊ ራዕዮች ጋር የማስተሳሰርን አላማም ይዟል።

ተለዋዋጭ በሆነው የዓለምና የቀጣናው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ አዳዲስ ስጋቶችንና መልካም አጋጣሚዎች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በመሆኑም ጉባኤው የሰብዓዊ መብቶች አስተዳደርን ማሻሻል፣ ጥሰትን መከላከል፣ እንዲሁም የተጠያቂነት አሠራርን በሚጨበጥ መንገድ ማጠናከር የሚያስችሉ ምክረ ሀሳቦች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ማዕከል በማድረግ፣ ቀደም ሲል የተመዘገቡ የሰብዓዊ መብት ድሎችን በማስጠበቅና የወደፊቱን አቅጣጫ በመተለም የቀጣናውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ የሲቪክ ምህዳር እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ የሰላም ግንባታ እና መፈናቀል፣ የአካባቢና የቴክኖሎጂ ለውጦች፣ ሰብዓዊ መብቶች በዲጂታል ዘመን እና አካታችነት፣ አፍሪካዊ ትርክቶች እና የተመዘገቡ ድሎችን ማስጠበቅ ውይይት እየተደረገባቸው የሚገኙ አጀንዳዎች ናቸው።

በጉባኤው የሁለተኛ ቀን ውሎ በሰላም እና ደህንነት ማዕቀፍ ውስጥ ተጠያቂነትን ማስፈን በሚል ርዕሰ ጉዳይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

የስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ የተጠያቂነት ባህል ማሳደግ፣ አፍሪካዊ የእውቀት ሥርዓቶችና የማኅበረሰብ ድምፆች ተሰማኒትን ማጉላት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክረ ሀሳቦች ይቀርባሉ።

የምሥራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በወረቀት ላይ ያሉ መብቶች በዜጎች እውነተኛ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ትርጉም ያለውና ዘላቂ ለውጥ ማምጣት ወደሚችሉበት ተግባራዊ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ መሠረት መጣል መሆኑ ተመላክቷል።

ጉባኤው ነገ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም