የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጥቂት ሀገራት ቡድን የሚወሰንበት ዘመን አብቅቷል-ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጥቂት ሀገራት ቡድን የሚወሰንበት ዘመን አብቅቷል-ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን
ሞስኮ፣ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጥቂት ሀገራት ቡድን የሚወሰንበት ዘመን አብቅቷል ሲሉ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለፁ።
ሶስተኛው የሩሲያ -አፍሪካ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በሞስኮ ከተማ ሲጀመር የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በንግግር ከፍተዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በንግግራቸው ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታሪካዊ ፣የሀገራትን ሉዓላዊነት ያከበረ፣በጋራ ተጠቃሚነት፣በወንድማማችነት እና መከባበር ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።
ይህ ትብብርም እየተጠናከረ የሚሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።
አፍሪካ እያሳየች ያለው የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ሚና እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።
የዚህ ማሳያ የሚሆነው ከዓለም 20 ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያሳዩ ካሉ ሀገራት ውስጥ 12ቱ በአፍሪካ የሚገኙ መሆኑ ነው ብለዋል።
ሩሲያም አፍሪካ በምግብ ራሷን እንድትችል የቴክኖሎጂ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማፋጠን ፣አህጉር አቀፍ የግብርና ፕሮግራሞችን ለማገዝ ዝግጁ ነች ነው ያሉት።
ይህም አፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነቷን እንድታረጋግጥና ከራሷ ፍጆታ በተጨማሪ ምርቶቿን ወደ ሌሎች ሀገራት መላክ እንድትችል የሚያግዝ ነው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን አፍሪካን “የወደፊቱ አህጉር” በማለት የገለፁ ሲሆን በዓለም አቀፍ ስርዓት ውስጥ የሚኖራት ተጽዕኖ የበለጠ እንደሚያድግ አብራርተዋል።
በመሆኑም ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ጋር የተያያዙ አካሄዶችን የሚከተሉ ሀገራት ሕጋዊ ያልሆኑ ማዕቀቦችን፣ኢኮኖሚያዊ ጫናን፣ የታሪፍ ጦርነቶችንና ማስፈራሪያዎችን በመጠቀም አፍሪካውያንን እንደገና ወደ ዕዳ ጥገኝነት ለመመለስ እየሞከሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም አፍሪካ ሁሉ አቀፍ ሉዓላዊነቷን ሊያስከብሩ የሚችሉ በተለይም አዳዲስ የክፍያ መንገዶችን መከተል ይኖርባታል ያሉ ሲሆን ሩሲያ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነች ነው ያሉት።
የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጥቂት ሀገራት ቡድን የሚወሰንበት ዘመን ማብቃቱን የጠቆሙት ፑቲን፣በዓለም አቀፍ ስርዓት ውስጥ አዳዲስ የኃይል ማዕከላትም እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከእነዚህ አዳዲስ ማዕከላት መካከል የብሪክስ አባል ሀገራት (BRICS) ቡድን አስፈላጊ ሥፍራ እንዳለውም ተናግረዋል።
ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ የብሪክስ አባል ሀገራት ምጣኔያዊ ዕድገት 40% መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የቡድን 7 አባል ሀገራትን ምጣኔ ሐብት እድገትን በ10% የሚበልጥ መሆኑን ገልጸዋል።