ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መጽሐፍ በሩሲያኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ በቃ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ በቅቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጽሐፉ የምረቃ መርሃ ግብር ላይ በአካል ተገኝተው በመካፈላቸው ታላቅ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።


 

ይህ ታሪካዊ ስኬት የመደመር ፍልስፍና ከኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀት ተነስቶ ዛሬ ላይ ድንበር በመሻገር ወደ መላው ዓለም እየሰፋ መሄዱን የሚያሳይ ህያው ማረጋገጫ መሆኑን አመልክተዋል።

መጽሐፉ ከዚህ ቀደም ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ በእንግሊዝኛ፣ በቻይንኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለብዙኃን አንባቢያን መድረሱን አውስተዋል።

አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሀሳብ በሰፊው የሩሲያኛ ተናጋሪ ደጃፍ መድረሱ የፍልስፍናውን ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ይበልጥ እንደሚያጎለብተው ተናግረዋል።

እርምጃው የመደመርን እሴቶችና ሀሳቦች ለሌሎች ሕዝቦች የሚያደርስ አዲስ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተው የበሰለ ሀሳብ እንዳላት በተግባር የሚያሳይ መሆኑንም ነው የገለጹት።


 

ሩሲያ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የሥነ ጽሑፍና የዕውቀት መማሪያ ምድር ሆና እንዳገለገለች ሁሉ፣ አሁን የኢትዮጵያ ሀሳብ በሩሲያኛ ቋንቋ ለሩሲያ አንባቢያን መድረሱ የዕውቀት ልውውጡን ሙሉ እንደሚያደርገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

ለዚህ ስኬት መሳካትና ለመጽሐፉ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የሩሲያ ቱዴይ (RT) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና አመራሮች ያደረጉትን ጥረትና ትጋት በከፍተኛ ደረጃ አደንቃለሁ ብለዋል።


 

ይህ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የኢትዮጵያን የበለጸጉ አገር በቀል እውቀቶች፣ ባህሎችና ፍልስፍናዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ይበልጥ ለማስተዋወቅና በሕዝቦች መካከል ጠንካራ የባህልና የሀሳብ ድልድይ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም