በሶማሌ ክልል በከተሞች የመሰረተ ልማትና አገልግሎት አሰጣጥ የማሻሻል ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል በከተሞች የመሰረተ ልማትና አገልግሎት አሰጣጥ የማሻሻል ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ጅግጅጋ፣ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል በከተሞች የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ የማሻሻል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ በበጀት አመቱ የከተሞችን ልማትና እድገት ለማፋጠን ለሚከናወኑ ተግባራት ማስፈጸሚያ 21 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን ቢሮው አስታውቋል ።
የክልሉ ከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ቢሮ ከክልሉ ከተማ አስተዳደሮች ጋር በበጀት አመቱ ሶስት ወራት የስራ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ አካሂዷል።
የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ ሹክሪ በወቅቱ እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት የከተሞችን ልማትና እድገት ለማፋጠን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
በበጀት አመቱ በክልሉ ከተሞች በዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት ማስፈጸሚያ 21 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን ተናግረዋል።
የክልሉ ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የሚያስችሉ የመሠረተ ልማትና አገልግሎት አሠጣጥ የማሻሻል ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በኮሪደር ልማት፣ በአገልግሎት አሠጣጥና በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎች ውጤታማ ተግባራትን የማስፋፋትና አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አመልክተዋል።
በዚሁ መሰረት በክልሉ አራት የከተማ አስተዳደሮች የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።
በጅግጅጋ ከተማም ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ስራ እንደሚጀመር አመልክተዋል።
በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ቀልጣፋ ለማድረግ በግንባታ ላይ የሚገኙ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ከተሞች የመንገድ፣ የውሀ፣ የመብራትና የኔትወርክ አገልግሎቶችን የማቀናጀትና የማዘመን ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል ።
በክልሉ ከተሞች በዕቅድና በፕላን የሚመሩበት የዲጂታል አሠራር ሥርዓት የመዘርጋት ተግባር ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው የከተሞች ማዘጋጃ ቤት አገልግሎትን በዲጂታል የታገዘ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል ።
የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሻፊ አህመድ በበኩላቸው የከተማውን አገልግሎት አሠጣጥ ሥርዓትን ቀልጣፋ የማድረግ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማ መሬት አስተዳደርና የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ዲጂታል የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎችን የማስፋፋት ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
በመድረኩ ላይ የክልልና የዞን የስራ ሀላፊዎችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።