ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሪደርና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪውን ዕድገት እያሳለጡ ነው

ወላይታ ሶዶ ፤ ጥቅምት 18/2019(ኢዜአ )፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሪደርና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪውን ዕድገት እያሳለጡ መሆናቸውን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ  በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሶስት ወራት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ287 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱም ተመልክቷል።

የቢሮው ኃላፊ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ዕምቅ አቅም በመለየትና በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

በተለይ በክልሉ የኮሪደርና የመሠረተ ልማት ሥራዎች የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪውን ዕድገት እያሳለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በዚህም በ2019 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ በወላይታ ሶዶ ዳሞታ ተራራ ኢኮ ቱሪዝም፣ በጌዴኦ ራኮ ተራራ፣ እንዲሁም በጋሞ ዞን ያሉ የተለያዩ መዳረሻዎች በአዲስ መልክ ለምተው ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል።

ይህም የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተው፣ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሦስት ወራት ከ2 ሚሊዮን 306 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸውንና ከ287 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አስረድተዋል።


 

ክልሉ የበርካታ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና አርኪኦሎጂያዊ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችና የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ መሆኑ ለዘርፉ ዕድገት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።


 

በክልሉ ያሉ የቱሪዝም አቅሞችን በጥናት የመለየት፣ የመመዝገብና የማልማት ሥራዎችን ከመከወን ባሻገር፣ የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የዲጂታል ቱሪዝም ግብይትና የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በወላይታ ሶዶ ከተማና አካባቢዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማትና ሌሎች መሠረተ ልማት ሥራዎች የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር የሆቴል ኢንዱስትሪው እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው ያሉት ደግሞ በወላይታ ሶዶ የሚገኘው የኃይሌ ሆቴል ሪዞርት ሥራ አስኪያጅ አቶ አላዛር ማዳ ናቸው።


 

"ቱሪስት በዋነኝነት የሚያየው መሠረተ ልማትን ነው" ያሉት አቶ አላዛር፣ ምቹ ማረፊያና የመሠረተ ልማት አማራጮች መኖራቸው ተጓዦች ክልሉን የጉዟቸው መዳረሻ አድርገው እንዲመርጡ እያደረገ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ አዳዲስ ሆቴሎች እየተመረቁ በመሆኑ የገበያ ውድድር ከመፍጠሩም በላይ ቱሪስቶች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ ሰፊ አማራጭ እየሰጠ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በዳሞታ ተራራ ኢኮ ቱሪዝም የካዎ ሎጅ ባለቤትና አስጎብኚ ወይዘሮ ኢየሩሳሌም መርዕድ በበኩላቸው፣ በዳሞታ ተራራ የተገነባው የኢኮ ቱሪዝም ደረጃ መወጣጫ በአካባቢው አዲስ የቱሪዝም መነቃቃት እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።


 

የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ተጠናቆ ክፍት መደረጉና ይህም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እንዲመጡ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሎጃቸው የጎብኚዎችን ቀልብ ይበልጥ ለመሳብ የሚያስችሉ አገልግሎቶች ላይ አተኩረው እየሠሩ መሆናቸውንም አስጎብኚዋ አክለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም