በክልሉ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገኘው መልካም ውጤት በበጋም ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገኘው መልካም ውጤት በበጋም ተጠናክሮ ይቀጥላል
ሚዛን አማን፣ጥቅምት18/2019 (ኢዜአ)-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገኘው ውጤት በበጋ ወራትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው የበጀት ዓመቱ የሦስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን የሚገመግም መድረክ በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩም ባለፉት የሦስት ወራት 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር መከናወኑና ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተመላክቷል።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አሰለፈች መብራቱ በመድረኩ እንደገለጹት ቢሮው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ደህንነት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ664 ሺህ በላይ ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የልማት ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
ከተከናወኑ የልማት ሥራዎች መካከል 900 የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳትና አዲስ ግንባታ ሥራዎች ይጠቀሳሉ ያሉት ቢሮ ኃላፊዋ፣ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በተያዘው የበጋ ወራትም ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ይህን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተሰጠ ትኩረት ከ25 ሺህ 300 በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሲሆኑ 7ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችም የገንዘብ ብድር ማግኘታቸውን ወይዘሮ አሰለፈች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የሴቶችን የቁጠባና የሥራ ባህል ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ከ11 ሺህ የሚበልጡ ሴቶች 54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር መቆጠብ መቻላቸውን ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ቢሮው በተጠቃሚዎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ውጤት የሚያመጡ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም አክለዋል።
የቢሮው የልማት ዕቅድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ሰሎሞን በበኩላቸው፤ ወጣቶች በበጎ አድራጎት ያሳዩትን ንቁ ተሳትፎ በሌሎችም ዘርፎች አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የሴቶችንና የወጣቶችን የቁጠባ ባህል ማሳደግ እና የፖለቲካና ወሳኔ ሰጪነት ተሳትፎን ማጠናከር የቢሮው አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አመልክተዋል።
በቤተሰብ አስተዳደር ሥርዓት ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ በተጨማሪ ሕጻናትን ከጥቃትና ከጉልበት ብዝበዛ መከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።