ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል በተለያዩ መስኮች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል- ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ሀይሉ (ዶ/ር) 

ሀዋሳ፤ ጥቅምት18/2019 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል ባለፉት ሦስት ወራት በተለያዩ መስኮች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የሲዳማ ክልል የፓርቲና የመንግስት ሥራዎቸ የ2019 በጀት ዓመት የሦስት ወራት አፈጻጸም ግምገማና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።


 

በውይይቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ሀይሉ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ባለፉት ሦስት ወራት በክልሉ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች የተከናወኑ ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው።

በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግና ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት በተሰራው ሥራ ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል።


 

ከተሞችን ለኑሮ ምቹ፣ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በሁሉም ከተሞች የኮሪደር ልማትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በትኩረት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በመደመር መንግሥት የተያዙ የልማት ውጥኖችን በላቀ ብቃት መፈጸም እንዲቻል አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ከማድረግ አንጻር የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

በመድረኩ የክልሉ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊዎች ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም