ቀጥታ፡

የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት ማዕከል አድርገዋል- አምባሳደር ደዋኖ ከድር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የወሰደቻቸው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚና የመዋቅር ለውጥ እርምጃዎች የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጋቸውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ የእስያ እና ፓሲፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር ገለጹ።

ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በተለይ ለውጭ ኩባንያዎች ሰፊ የንግድና የኢንቨስትመንት እድል እየከፈተ ይገኛል።

የውጭ ምንዛሬ ተመንን ወደ ገበያ መር ሥርዓት ማሸጋገርና የንግድ መሰናክሎችን መቀነስ የውጭ ባለሀብቶች በሀገሪቱ ገበያ ላይ ያላቸውን እምነት አሳድጎታል።

ይህንን ተከትሎ የውጭ ኩባንያዎች ኢንቨስትመንታቸውን እያሰፉ ከመሆናቸውም በላይ አዳዲስ የንግድ አጋርነቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ የእስያ እና ፓሲፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነች ያለው ሥራ አዎንታዊ ውጤት እያስገኘ ነው፡፡

በርካታ የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንታቸውን ለመጀመርና ለማሳደግ፣ እንዲሁም የንግድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያላቸው ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም አመልክተዋል።

ዳይሬክተር ጄኔራሉ አክለውም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት  ብቻ ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ከ180 በላይ ኩባንያዎች በሀገሪቱ የሚገኙ የኢንቨስትመንት እድሎችን መመልከታቸውን አስታውቀዋል።

እነዚህ ከእስያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ የመጡ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን መጎብኘታቸው ሀገሪቱ ያላትን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና ሳቢነት የሚያሳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መካከለኛው ምስራቅና እስያ ለኢትዮጵያ ቡና እና ልዩ ልዩ የግብርና ምርቶች የኤክስፖርት ገበያ መዳረሻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም