ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶችን ከሩሲያ ተረከበች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18 /2019 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች (Su-35 4++ Generation) ከሩሲያ መረከቧን ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ዛሬ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በመከላከያ ኃይል እያደረገች ያለው ዝግጁነት ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አቅም እያላበሳት መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ከሩሲያ መንግስት ጋር በደረስነው ስምምነት መሰረት፣ ዛሬ የመጀመሪያዎቹን አስራ ሁለት የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች (Su-35 4++ Generation) ተረክበናል ብለዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ አራት የኤስ-400 (S-400) የአየር መከላከያ ስርዓት ባትሪዎችን ትረከባለች ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው ወዳጄ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከስምምነታችን አንድ ዓመት አስቀድሞ እነዚህን የጦር አውሮፕላኖች እንድንረከብ ስላሳዩት ትጋት ላመሰግናቸው እወዳለሁ ብልዋል።

እነዚህን የጦር ጄቶች በመታጠቅ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ሆናለች ሲሉም ገልጸዋል።

ይህ ታሪካዊ ስኬት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ይበልጥ የሚያጠናክር ሲሆን፣ ወደፊትም የጋራ ደህንነታችንን እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ በልበ ሙሉነት እንድንቀጥል ትልቅ አቅም ይሆነናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም