በአዳማ ከተማ አስተዳደር በመኸር አዝመራ ከለማው 24 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ውሰጥ 90 በመቶ ሰብል ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ አስተዳደር በመኸር አዝመራ ከለማው 24 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ውሰጥ 90 በመቶ ሰብል ተሰብስቧል
አዳማ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ አስተዳደር የደረሰ ሰብልን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል 90 በመቶ የሚሆነው በዘመቻ መሰብሰብ መቻሉን የአስተዳደሩ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማ አስተዳደሩ በ2018/019 የምርት ዘመን 24 ሺህ 900 ሄክታር መሬት በተለያዩ ዓይነት አዝርእቶች ለምቷል።
በመኸሩ የለማውን ሰበል ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሰብል ማሰባሰብ ዘመቻው ዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ 15 ኮምባይነሮችን ጨምሮ ተማሪዎችንና የጸጥታ አካላት እንዲሁም በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ 90 በመቶ ያህል የደረሰ ሰብል መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮችም በልማት ቡድኖችና በአደረጃጀት ታግዘው ምርታቸውን በደቦ እያሰባሰቡ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ መከላከል መቻላቸውን አስረድተዋል።
ቀሪው ሰብል የማሰባሰብ ስራው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ እስከ ሚቀጥለው ሳምንት ለማጠናቀቅ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮችም የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ በተቀናጀና በተሟላ ዝግጅት እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑንም ኋላፊው ተናግረዋል።
ለምርት የደረሱ የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የጤፍና ሌሎች የሰብል ዓይነቶችን ከብክነት ለመከላከል እንዲቻልም አነስተኛ ማሽነሪዎች እና ኮምባይነሮች በበቂ ሁኔታ ስምሪት መደረጉን አብራርተዋል።