የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለጋራ ዕድገትና ለቀጣናው ሰላም ወሳኝ ነው - የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለጋራ ዕድገትና ለቀጣናው ሰላም ወሳኝ ነው - የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የቀጣናውን የጋራ ዕድገት፣ ሰላምና ደህንነት የሚያጠናክር በመሆኑ ጎረቤት ሀገራት በሰከነ መንገድ ተረድተው ለውይይትና ድርድር መቀመጥ አለባቸው ሲሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አሳሰቡ።
ኢትዮጵያና ቀይ ባህር ለዘመናት ተነጣጥለው መኖር አይችሉም፤ ቀይ ባህርም ለኢትዮጵያውያን የህልውና መሰረት ነው።
ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ባህልና ህግ ቀይ ባህር የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት የንግድና ስልጣኔ መሰረት መሆናቸውንም ያረጋገጣሉ።
የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት፣ 130 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባትና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኝ የባሕር በር የሌላት ሀገር ናት።
ይህ ታሪካዊ ጠባሳ ነው ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ ከቀይ ባህር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በመሬት ተከልሎ መኖር ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1880ዎቹ አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት በዘመቱ ወቅት የተተከለ የጊዜ ቦምብ መሆኑን ገልጸው፤ ጥያቄው ምላሽ ካላገኘ ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገሩ አይቀርም ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ ነው ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ እንዴት ይመለስ በሚለው ላይ ሁሉም መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ጎረቤት ሀገራትም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በመገንዘብ አብሮ ለማደግ፣ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ነገር ለማስረከብ መሆኑን በሰከነ መንገድ ተረድተው ለውይይትና ድርድር መቀመጥ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ በጎረቤት ሀገራት ዘንድ ለጋራ ልማትና ዕድገት ወሳኝ ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳታገኝ የሚፈልጉ አካላት መነሻ ሀገራችን የቀጣናው መልህቅነቷንና ሀያልነቷን አስጠብቃ እንዳትቀጥል ከማድረግ የሚመነጭ ክፋት መሆኑን ገልጸዋል።
ግብጽ "የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳኛል እስከ 20 ዓመት በሚቆይ ጊዜ ይሞላ" የሚል ክርክር ታቀርብ እንደነበር አስታውሰው፤ ነገር ግን በአራት ዓመት ውስጥ የበለጠ ውሃ አግኝታ ሙሌቱ ተጠናቋል ብለዋል።
"ጅብ በጨረቃ ያባረረው ውሻ በቀን ወደ ውጭ አይወጣም" እንዲሉ ከመፍራት ይልቅ እውነታውን ማየት እንደሚገባም አሳስበዋል።