አፍሪካ ፍትሃዊ የሆነ የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር የምታቀርበውን ጥያቄ ራሽያ ትደግፋለች-ማሪያ ዛካሮቫ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ ፍትሃዊ የሆነ የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር የምታቀርበውን ጥያቄ ራሽያ ትደግፋለች-ማሪያ ዛካሮቫ
ሞስኮ፣ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦የአፍሪካዊያን ሀገራት የበለጠ ፍትሃዊ የሆነ የዓለም ስርዓት ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ራሽያ ከጎናቸው ሆና እንደምትደግፍ የራሽያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ገለፁ።
የራሽያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ነገ የሚጀመረውን 3ኛው የራሽያ-አፍሪካ ጉባዔ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ከአፍሪካ ጋር ከሶቪየት ህብረት ዘመን ጀምሮ የዘለቀ አጋርነት አለን ብለዋል።
አፍሪካ እየተለወጠ ባለው የአለም ስርዓት ውስጥ የሚገባትን ቦታ ማግኘት አለባት ያሉት ማሪያ ዛካሮቫ ፣ አሁን ያለንበት ዘመን ጥቂት ኃያላን ብቻ ውሳኔ ሰጪ የሚሆኑበት አይደለም ነው ያሉት።
ይህ አካሄድ ይበልጥ ፍትሃዊ፣ሁሉንም የሚያሳታፍ እና የብዙኃንን ድምጽ የሚያከብር ወደሆነው የባለብዙ ዋልታ የዓለም ስርዓት መሸጋገር አለበት የሚለውን የአፍሪካ ጥያቄ ሀገራቸው ተደግፋለች ብለዋል።
የቅኝ ግዛት ዘመን ፖሊሲዎች መቀየር እንዳለባቸው ገልፀው፣ ይህም እያንዳንዱ ሀገር የራሱን የውስጥ ጉዳይ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና የባህል እሴት በነጻነት የመወሰን መብት ሊያረጋግጥ የሚገባ መሆን አለበት ነው ያሉት።
አፍሪካ በራሽያ የውጭ ፖሊሲ ውስጥ ቁልፍ ቦታ እንዳላት ጠቁመው ፣በዚህም የአፍሪካ ሀገራት የበለጠ ፍትሃዊ የሆነ የዓለም ስርዓት ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት ከጎናቸው መሆኗ ተደንግጓል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ማሪያ ዛካሮቫ አክለውም ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር የምታደርገው ትብብር በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚደረግ ሁለገብ ትብብርን፣የሁለትዮሽ ግንኙነትን እና ቀጣናዊ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።
ትብብሩ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ነው ያሉ ሲሆን ይህ አጋርነት የንግድ ልውውጥ መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያድግ አድርጎታል ብለዋል።
ራሽያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን አጋርነት እያጠናከረች ባለችበት በዚህ ወቅት እንደ አውሮውፓውያን አቆጣጠር በ2025 ብቻ የንግድ ልውውጥ መጠኑ ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን ገልፀዋል።
በዚሁ ዓመት ከ18 ሚሊዮን ቶን በላይ እህል ለአፍሪካ አህጉር ማቅረቧን የገለጹ ሲሆን ትብብሩ በኃይል፣ በኢንዱስትሪ፣ በትምህርት እና በሌሎችም ዘርፎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ብለዋል።