የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ስልቶች የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ አቅም እየገነቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ስልቶች የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ አቅም እየገነቡ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ስልቶች የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ እመርታዊ ስኬት እያስገኙ መሆናቸውን የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር ዴኤታ አባስ መሐመድ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከአፍሪካ የምግብና የግብርና ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አህጉራዊ የግብርና ፖሊሲ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት የሚቆየው 13ኛው ዓመታዊ አህጉራዊ የባለድርሻ አካላት ጉባኤው ”ተወዳዳሪ የምግብና ግብርና ኢኮኖሚን መገንባት፤ ለአፍሪካ የፖሊሲ፣ የንግድና የኢንዱስትሪ ልማት መንገዶች” የሚል መሪ ሃሳብ ተሰጥቶታል።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር ዴኤታ አባስ መሐመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የውስጥ ፍጆታን በመሸፈን ከስንዴ አስመጪነት ወደ ራስ መቻል አሸጋግሮናል ብለዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብርም የወተት፣ የዶሮ፣ የንብ፣ የዓሳ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም መገንባቱን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዘመቻም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ውጤታማነትን በማጠናከር ለዘላቂ የግብርና ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የግብርና ምርታማነትም አፍሪካ ግዙፍ የግብርና አቅምና ጸጋዋን ወደ ተወዳዳሪ ምርታማነት በማሸጋገር አህጉራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የአፍሪካን የግብርና ምርታማነት በማሻሻል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢንዱስትሪ የእሴት ሰንሰለት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ ጸጋ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የግብርና ፖሊሲ ማሻሻያዎች ዘርፉን ወደ ዘመናዊና በገበያ ወደሚመራ አሰራር አሸጋግሯል ብለዋል።
ከታክስ ነፃ የማሽነሪዎች ግዥ፣ የዲጂታል ገበያ፣ የመስኖ ልማትና የገበያ ማሻሻያዎች ለአግሮ-ፕሮሰሲንግና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሀገራትም የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ስልቶች በልምድና ተሞክሮነት በመጋራት የጋራ ዕድገትና ብልፅግናን የሚያረጋግጥ ሥርዓት መከተል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የአፍሪካ የምግብና የግብርና ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አንድሩ ቴሙ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ የግብርና ፖሊሲዎች በአህጉሪቱ እውነቶች ላይ መመስረት አለባቸው ብለዋል።
የአጠቃላይ የአፍሪካ ግብርና ልማት መርሃ ግብርና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት (AfCFTA) ማዕቀፎች የአህጉሪቱ ግልጽ የዕድገት ማሳለጫዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የምግብና የግብርና ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አንቶኒ ቻፖቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግብርና ስርዓትን ለማሻሻል የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የባለድርሻ አካላት ጉባኤውም የአፍሪካን የግብርና ምርታማነት የሚያልቁ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ምክረ ሀሳቦችን በመለዋወጥ ተጨባጭ የፖሊሲ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።