ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ይሰራሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፣ በኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር አብደላ ሀሰን አልሻምሲ ጋር በሁለትዮሽ ወታደራዊ እና የልማት ትብብርን አስመልክቶ ውይይት አካሂደዋል።


 

ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እየሠሩባቸው ባሉ ወታደራዊ መስኮች ላይ ያላቸውን አጋርነቶች አንስተዋል።

በተለይም የመከላከያ ሚኒስቴር በልማት ድርጅቶቹ በኩል እያከናወናቸው በሚገኙ ውጤታማ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እያደረገች ያለውን ጉልህ አስተዋፅኦ እና ወሳኝ ድጋፍ አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር አብደላ ሀሰን አልሻምሲ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበች ላለችው ፈጣን እና ሁለንተናዊ የልማት እድገት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

አምባሳደሩ፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የልማት ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መስራት መቻላቸውን እና ለተመዘገቡት ስኬቶችም እንደ እውነተኛ ስትራቴጂካዊ ወዳጅ ሀገር የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ትልቅ ኩራት እንደሚሰማቸውም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸው ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የሁለትዮሽ ወዳጅነት መገንባታቸው ተመላክቷል።

ይህንን አጋርነት ወደ ላቀ እና ዘላቂ የወታደራዊ ትብብር ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት ለመስራት መስማማታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ መረጃ ያመለክታል።

#ትልቅሀገር፣ #ትልቅሕዝብ፣ #ታላቅርዕይ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም