ግብፅ ለሱዳን ወታደሮች የተከለከሉ የኬሚካል ጦር መሣሪያ አጠቃቀም ስልጠና እየሰጠች ነው - ግብፃዊው ጸሐፊ ሞሐመድ ሳድ ኪራላ - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ ለሱዳን ወታደሮች የተከለከሉ የኬሚካል ጦር መሣሪያ አጠቃቀም ስልጠና እየሰጠች ነው - ግብፃዊው ጸሐፊ ሞሐመድ ሳድ ኪራላ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ የግብፅ መንግሥት የሱዳን ወታደሮችን የተከለከሉ የኬሚካል ጦር መሣሪያዎችን እንዲጠቀሙ እያሰለጠነ ነው ሲሉ ታዋቂው ግብፃዊ የፖለቲካ ጸሐፊና አክቲቪስት ሞሐመድ ሳድ ኪራላ ገለጹ።
የግብፅ አየር ኃይል በሱዳን ግዛት ውስጥ በሚገኙ የወርቅ ማዕድን አውጪዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙንና ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
የሱዳን ታጣቂ ኃይሎች (SAF) በፈጣን ደጋፊ ኃይሎች (RSF) ላይ የተከለከሉ የኬሚካል መሣሪያዎችን (በዋናነት የክሎሪን ጋዝ ተብሎ የተጠረጠረውን) ተጠቅመዋል በሚል አሜሪካ በሱዳን መንግስት ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
አሜሪካ እ.ኤ.አ ጁን 2025 የመጀመሪያ ዙር የኤክስፖርት እና የፋይናንስ ማዕቀቦችን የጣለች ሲሆን፣ እ.ኤ.አ ጁላይ 2026 ደግሞ የአቪዬሽን እና የዓለም አቀፍ ብድር ገደቦችን የያዘ ተጨማሪ ማዕቀብ በሱዳን ላይ ጥላለች።
ታዋቂው ግብፃዊ የፖለቲካ ጸሐፊና አክቲቪስት ሞሐመድ ሳድ ኪራላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የግብፅ ጦር የሱዳን ወታደሮችን በገዛ ወገናቸው ላይ የኬሚካል መሣሪያ እንዲጠቀሙ ማሠልጠኑ አሳዛኝ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እነዚህን የጦር ወንጀሎች በሚገባ በመሰነድ ጥፋተኞችን ለሕግ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።
ጸሐፊው በቅርቡ በጉልበታቸው የሚተዳደሩ ንጹሀን የሱዳን የወርቅ ማዕድን አውጪዎች ላይ የተፈጸመውን የአየር ጥቃት አጥብቀው ኮንነዋል።
ጥቃቱ ከግብፅ ወሰን ከ44 እስከ 46 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ሱዳን ግዛት ዘልቆ መፈጸሙን የጠቀሱት ጸሐፊው፣ ድርጊቱ የሱዳንን ሉዓላዊነት በግልጽ የጣሰ ነው ብለዋል።
የግብፅ አየር ኃይል እ.ኤ.አ ጁን 16 እና ኦክቶበር 10/ 2026 በሱዳናውያን ንጹሐን ዜጎች ላይ ድንገተኛ የአየር ጥቃት አድርሷል።
ድርጊቱ የካይሮን እውነተኛ ፍላጎትና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የወደፊት ግንኙነት አስመልክቶ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
የግብፅ መንግሥት ጥቃቱን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ፣ ማዕድን አውጪዎቹ የግብፅን ድንበር ጥሰው በመግባታቸው በገዛ ግዛታችን ውስጥ እርምጃ ወስደናል" ሲል ገልጿል።
ሆኖም ኪራላ ይህን ምክንያት ውድቅ ያደረጉ ሲሆን ድርጊቱ በቪዲዮ ከተቀረጸው ማስረጃ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጋጭና መሰረተ ቢስ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ማዕድን አውጪዎቹ ወርቅ ለመፈለግ ወደ ግብፅ ግዛት ለመድረስ ረጅም ርቀት በእግር ተጉዘዋል የሚለው አባባል ከፍተኛ ጥርጣሬን የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት ኪራላ ግብፅ ለጉዳዩ የሰጠችው ማብራሪያ ከንቱ መሆኑን አስረድተዋል።
አክለውም የማዕድን አውጪዎቹ ዜግነት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ቢሆኑም እንኳ፣ የትኛውም አገር በሌላ ሉዓላዊ አገር ወሰን ውስጥ ዘልቆ ወታደራዊ ጥቃት የማድረስ ሕጋዊና ሞራላዊ መብት የለውም ብለዋል።
በመሆኑም እንደዚህ ያሉ ከባድ የሕግ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ያለ ማንም ተጠያቂነት ፈጽሞ በዝምታ ሊታለፉ እንደማይገባ አስገንዝበዋል።
በግብፅ ወታደራዊ ተቋም ውስጥ ያሉ አንዳንድ አካላት ከሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች ጋር በመመሳጠር የሱዳንን የተፈጥሮ ሀብትና ወርቅ ለመዝረፍ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።