ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የድንገተኛና የአደጋ ጊዜ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን አቅም ገንብታለች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የድንገተኛና የአደጋ ጊዜ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በአፍሪካ ቀዳሚና ምሳሌ የሚሆን አቅም መገንባቷን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ 

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ድንገተኛና ፅኑ እንክብካቤ ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር "አጣዳፊ የሕክምና እርዳታ ለሁሉም ከሕክምና ቦታ እስከ ዲጂታል ሥርዓቶች መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የድንገተኛ ሕክምና ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል። 


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልእክት፤ በኢትዮጵያ የድንገተኛና የፅኑ ሕክምና አገልግሎት በማዘመን ሕይወትን የማዳን አቅምን እየተገነባ ነው ብለዋል። 

በዚህም የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትና አደጋዎችን በብቃት በመወጣት በአፍሪካ ቀዳሚና ምሳሌ የሚሆን አቅም በመገንባት በወረርሽኞች ወቅት ሕይወትን የመታደግ አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጋለች ብለዋል። 

ከዓመታት በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ ደካማ የፅኑ ሕክምና (ICU) እና የኦክስጅን የማምረት አቅም በከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማሻሻል የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚችል አቅም መገንባቱን ገልጸዋል። 


 

በአምስት ዓመታት ውስጥ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካዎችን ቁጥር ከ2 ወደ 56 በማሳደግ የመቶ ኪሎ ሜትር ራዲየስ አቅርቦትን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት ከአምስት መቶ በላይ ሆስፒታሎች እና ከሦስት ሺህ በላይ ጤና ጣቢያዎች የድንገተኛ ሕክምና አቅምን ለማጠናከር፣ የእናቶችና ሕፃናት የሞት መጠንን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል። 

በትራፊክ አደጋዎች የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የተቀናጀ የሪፈራልና የአምቡላንስ አገልግሎትን የማጠናከር ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። 


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ድንገተኛ ሕክምና ፈጣንና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎትን ማቅረብ የሚጠይቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል። 

ዩኒቨርሲቲው በአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ የሕክምና ትምህርትን፣ ምርምርንና የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን አቀናጅቶ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። 

ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልንና የጤና ሳይንስ ኮሌጅን በማቀናጀት የድንገተኛ ህክምና አቅምን የማሳደግ ስራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። 


 

የኢትዮጵያ ድንገተኛና ፅኑ እንክብካቤ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ወልደሰንበት ዋጋው እንዳሉት፤ የዓለም አቀፍ የድንገተኛ ሕክምና ኮንግረስ በአፍሪካ ሲካሄድ የመጀመሪያው ነው። 

ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ አፍሪካ በዘርፉ የዳር ተመልካች ሳትሆን ለዓለም አቀፍ የሳይንስና የምርምር ዕድገት የበኩሏን አስተዋጽኦ የምትወጣበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል። 


 

በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ በበኩላቸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚሊዮኖች ሕይወት በድንገተኛ አደጋ እንደሚቀጠፍ ገልጸዋል። 

በተለይም አፍሪካ ከዓለም ሕዝብ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋና የድንገተኛ ሕክምና ተግዳሮቶች የሚስተዋሉባት አህጉር መሆኗን አመልክተዋል። 

ኢትዮጵያ የፅኑ ህሙማን እንክብካቤን ለማሻሻል እያደረገችው ያለውን ጥረት በማድነቅ፤ በተለይም ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም