የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም (NEP-3.0) ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም (NEP-3.0) ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ ከዋናው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በርቀት የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም (NEP-3.0) ይፋ ሆኗል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
ፕሮግራሙ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በማስፋት የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን የኃይል ዋስትና ለመገንባት እንደሚያግዝ ተገልጿል።
''ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ ሳይንሳዊ መሠረት ያላቸውን ፖሊሲዎችና አጋርነቶችን ማሳደግ'' በሚል መሪ ኃሳብ የተዘጋጀው 3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት እየተካሄደ ነው።
በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም መካሄዱን በቀጠለው መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም “NEP-3.0” ይፋ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ፕሮግራሙ የኃይል አቅርቦትና ምርታማነትን በማሻሻል የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያለመ ነው።
በተለይም የግብርና ምርት ማቀነባበር፣ የኢንዱስትሪና የዲጂታል መሰረተ ልማት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎትን በማሟላት ምርትና አገልግሎትን ለማስፋፋት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም የኢትዮጵያን የ65 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን የበለጠ ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ፣ የልማት አጋሮችና የማኅበረሰቡን ትብብር በማቀናጀት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ከዋናው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በርቀት የሚኖሩ የገጠርና ሩቅ አካባቢ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አነስተኛ የኃይል ማመንጫና የኃይል ማከፋፈያ ሥራዎች እንደሚሰሩ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምታመነጨው ኤሌክትሪክ ከአየር ብክለት የጸዳና ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።
የኃይል ምንጮችን ማብዛትና የፀሐይና የጂኦተርማል ኃይልን በማሳደግ የኃይል ዋስትናን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ዳቢ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም (NEP-3.0) የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ የቴክኖሎጂ፣ የትግበራ ስልቶችንና የፋይናንስ አማራጮችን ያካተተ ስትራቴጂ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮግራሙም ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በርቀት የሚገኙ አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በፈረንጆቹ እስከ 2035 ድረስ የሚተገበር ነው ብለዋል።
ፕሮግራሙን ለመተግበርም ከዋናው የኃይል ማስተላለፊያ በርቀት የሚኖሩ ዜጎችን የገጠር አካባቢ ገጽታ በጎግል ካርታ በመለየት የገጠር አካባቢ የፀሐይ፣ የነፋስና የውሃ ኃይል ሀብት በመተንተን ተመራጭ የኃይል ቴክኖሎጂዎችን ለመለየት መሰራቱን አመልክተዋል።
የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራሙንም በጥብቅ የቁጥጥር ማዕቀፍና ማበረታቻ በመምራት የዜጎችን የኃይል አቅርቦት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በዚህም የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በማስፋፋት የገጠር ኢኮኖሚን ለማነቃቃት፣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ፍሰትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።