በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል
አሶሳ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ሦስት ወራት በግብርና፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የክልሉን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግመዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት በግብርና፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የክልሉን የመልማት አቅም በተግባር ያሳዩ ናቸው።
በተለይም የማዕድን ዘርፉን ለማልማት በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸው፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 3 ሺህ 833 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን ጠቅሰዋል።
ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ አምራቾች ሕጋዊ መንገድን በመከተል ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ይጠናከራል ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ የበጋ መስኖ ልማትን በማጠናከር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ውጤታማ ተግባራት እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።
በገቢ አሰባሰብ ዘርፍ የታየውን መነቃቃት በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር አሰባሰብ ሂደትን በመከተል የገቢ አቅምን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ የወጣቶችን ተሳትፎ ማጎልበት፣ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስፋፋትና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚኖረውን ድርሻ ማጠናከር እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
በቀጣይም ባለፉት ሦስት ወራት የተከናወኑ ውጤታማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በማስቀጠል ተጨባጭ ውጤት የማስመዝገቡ ተግባር ይጠናከራል ብለዋል።