ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲጂታል መሰረተ ልማት ለቀጣናዊ የንግድና ኢንቨስትመንት መሳለጥ ተምሳሌታዊ የትብብር ምኅዳር ፈጥሯል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዲጂታል መሰረተ ልማት በሁሉም ዘርፍ ቀጣናዊ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያሳልጥ ተምሳሌታዊ የትብብር ምኅዳር መፍጠሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) ሀገራዊ የዲጂታል መሰረተ ልማትና የፋይናንሲንግ ሞዴሎች የምክክር መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።


 

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፈንድና ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታገስ ሙሉጌታ በዚሁ ወቅት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እያሻሻለ ነው ብለዋል።

ስትራቴጂውም የፋይናንስ፣ የንግድ፣ የፈጠራና ተያያዥ የአገልግሎት ተደራሽነት አማራጮችን በማስፋት ዘመናዊና የተሳለጠ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታና ሕዝብ አገልግሎቶችን እያፋጠነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል መሰረተ ልማት በሁሉም ዘርፍ የሀገር ውስጥና ቀጣናዊ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ ተምሳሌታዊ የትብብር ምኅዳር መሆኑን ተናግረዋል።

በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የተከናወኑ ዘመናዊ አሰራሮችም የድንበር ተሻጋሪ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና ትብብርን በማፋጠን ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን አስረድተዋል።


 

የድንበር ተሻጋሪ ዲጂታል የንግድ ሥርዓት፣ የክፍያ አማራጮችና የሎጂስቲክስ አሰራሮች መዘመናቸው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት (AfCFTA) ትግበራን በማቀላጠፍ አህጉራዊ ኢኮኖሚ ውህደትን የሚያሳልጥ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል መሰረተ ልማት ተደራሽነትም ለንግድና ኢንቨስትመንት አካታች የአገልግሎት ምኅዳርን በመፍጠር የኢኮኖሚ ትብብርን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ ከምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያና አባል ሀገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ትብብር በመገንባት በትኩረት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

መድረኩም የኮሜሳና አባል ሀገራትን የዲጂታል መሰረተ ልማት ልምድና ተሞክሮ በማስፋት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያልቅ ትብብር ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።


 

የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ የቴሌኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ሊዮናርድ ቺቱንዱ በበኩላቸው፤ የዲጂታል መሰረተ ልማት አካታችና ቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስርን ለማጎልበት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተለይም የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰትና ትብብርን በማጎልበት ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብርን ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህም በቀጣይ የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በማስፋት የቴክኖሎጂ ፈጠራን የሚያጎለብትና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳልጥ ምኅዳር ለመፍጠር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም