በክልሉ ከተሞችን ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ የማድረጉ ጥረት በላቀ የህብረተሰብ ተሳትፎ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከተሞችን ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ የማድረጉ ጥረት በላቀ የህብረተሰብ ተሳትፎ ይጠናከራል
ዲላ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተሞችን ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ የማድረጉ ጥረት በላቀ የህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ በዲላ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮርደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅት ኢንጂነር ወንድሙ እንዳሉት፤ በከተሞች ለማህበረሰቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ውጤታማ የልማት ተግባራት ሲከናወኑ ቆይቷል።
በተለይ የኮሪደር ልማት የከተሞችን የተጎሳቆለ ገጽታ በመቀየር የተፋጠነ ሀገራዊ እድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልጸው፣ ለዚህም የዲላ እና የይርጋጨፌ ከተሞች ጥሩ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በክልሉ ከተሞችን ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ የማድረጉ ጥረት በላቀ የህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
ለዚህም የውስጥ ገቢን ከማሳደግ ጀምሮ ሁሉን የልማት አቅሞች አቀናጅቶ መምራት እንደሚገባ ተናግረው፣ የክልሉ መንግስት በየደረጃው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በከተማው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማትን ጨምሮ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ ናቸው።
በተለይም የኮሪደር ልማትን ማጠናከር፣ የከተማ ጽዳትና ውበት፣ የገቢ አቅምን ማሳደግና የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ ማጠናከር ትኩረት የተደረገባቸው ተግባራት ናቸው ብለዋል።