በትግራይ ክልል የንግድ እንቅስቃሴን የማነቃቃት እና ገበያን የማረጋጋት ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የንግድ እንቅስቃሴን የማነቃቃት እና ገበያን የማረጋጋት ስራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የንግድ እንቅስቃሴን የማነቃቃት እና ገበያን የማረጋጋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በክልሉ የፌዴራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) ገለጹ።
በክልሉ ሰላም እንዲጸና እና የመልሶ ግንባታ ስራዎች እንዲጠናከሩ የፌዴራል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በትግራይ ክልል የፌዴራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የባለአደራ አስተዳደር ከተቋቋመ ጀምሮ የተጎዱ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ መዋቅሮችን በመዘርጋት እና ችግሮች በማቃለል ህዝቡን ወደ መደበኛ ህይወቱ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
በትግራይ ክልል በሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ምክንያት ተቋርጠው የቆዩ መደበኛ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመሰረተ ልማት አውታሮች ወደ መደበኛ ስራቸው መመለሳቸውን ዶክተር ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡
በሕገ ወጡ ሕወሓት የፈረሱ የመንግስት መዋቅሮችን መልሶ ለመዘርጋት እና የሕዝብ አገልግሎቶች ለማስቀጠል ጊዜያዊ አስተባባሪዎችን በመመደብ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ገበያ እንዲነቃቃ እና የምግብና የምግብ ነክ ሸቀጦች እንዲሟሉ ባለአደራ አስተዳደሩ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም የአቅርቦት እጥረቱ እየተቀረፈ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የህዝብ የንቅናቄና የውይይት መድረኮች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የተናገሩት ዶክተር ቴዎድሮስ፤ በየመድረኩ የሚነሱ የህብረተሰቡን ፍላጎቶችና ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ ለችግሮች ምላሽ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
የፍጆታ አቅርቦትን ለማሟላትና የንግድ እንቅስቃሴን ለማነቃቃት እና ገበያን ለማረጋጋት ከባለሃብቶች፣ ባንኮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት የምግብ እና የምግብ ነክ ዓይነቶች ወደ ክልሉ እየገቡ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመቐለ ከተማ አስተዳደር የተጀመረውን የመማር ማስተማር ሂደት በሁሉም አካባቢዎች ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር ቴዎድሮስ አመልክተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ሰላም እንዲጸና እና የመልሶ ግንባታ ስራዎች እንዲጠናከሩ የፌዴራል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡