ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን አይበገሬነት ያጸና የህዝብ አለኝታ ነው

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ፈተናዎችን በጽናትና በድል አድራጊነት በመሻገር የኢትዮጵያን አይበገሬነት ያጸና የህዝብ አለኝታ ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

119ኛው የሠራዊት ቀን "የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሐሳብ በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።


 

ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ የሚያጋጥሟትን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች በሠራዊቷ አይበገሬ ጽናትና ቁርጠኝነት በማለፍ ክብሯና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ዘመናትን የተሻገረች ሀገር ናት።

ሠራዊቱ ፈተናዎችን በጽናትና በድል አድራጊነት በመሻገር የኢትዮጵያን አይበገሬነት ያጸና የህዝብ አለኝታ ነው ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት አሁንም ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚያስቡ የውስጥና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን እኩይ ሕልምና ሴራ በማክሸፍ የሀገር አለኝታነቱን በተግባር እያስመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ሠራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ክብርና ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ ለትውልድ በማሻገር አኩሪ ገድል እየፈጸመ የሚገኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንዲሁም ከክልሉና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በክልሉ የሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ እያሳየ ላለው ቁርጠኝነት ርዕሰ መስተዳድሯ ምስጋና አቅርበዋል።

ዕለቱን "የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሐሳብ በጋራ ስናከብር የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ታላቅ ኩራት ይሰማዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሯ፣ የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ እንደወትሮው ለሠራዊቱ ያለውን ደጀንነት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


 

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሙላቱ ጀልዱ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያ ሠራዊት ዘመናዊ ባልሆኑ ትጥቆች የውጭ ወራሪን አሳፍሮ መመለሱን ገልጸው አሁን ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ታጥቆ ሌላ ጀብዱ እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል። 

አሁን ላይ የሚሰጠውን የግዳጅ ተልዕኮ በአጭር ጊዜ ውስጥ በላቀ ብቃት የመፈጸም አቅሙን በእጅጉ ማሳደጉንም ገልጸዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ የሠራዊቱን አመሠራረት የሚዳስስ የመነሻ ጽሑፍ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም