ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መርሐግብር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አቅም እየሆነ ነው

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሃግብር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋትና ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅም እየሆነ መምጣቱን የክልሉ እንስሳት ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮ ሃላፊው አቶ አሰፋ ፎና ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራ በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው፡፡


 

መርሃ ግብሩ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋትና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅም መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት ለማምረትም እያስቻለ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ በወተት፣ በዶሮ፣ በንብ ማነብ፣ በአሣ እርባታ፣ በሃር ትል እንዲሁም በግና ፍየሎችን በማድለብ ሥራ የተደራጁ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

የወተት ሃብት ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሥራ መሰራቱን ገልጸው፣ በዚህ በኩል ባለፉት አራት ዓመታት የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ላሞችን ቁጥር ከ6 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 21 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።


 

በተያዘው ዓመትም የላሞችን ዝርያ የማሻሻል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ አሰፋ፣ ከ837 ሺህ ቶን በላይ ወተት ለገበያ የማቅረብ ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

በዶሮ እርባታም የእንቁላል ምርታማነትን በማሳደግ ገበያን ለማረጋጋትና የአመጋገብ ሥርዓትን ለማስተካከል የተያዘውን ግብ ለማሳካት ዘንድሮ በክልሉ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዶሮ ለህብረተሰቡ ይሰራጫል ብለዋል።

በንብ ማነብ ሥራ ለኢንዱስትሪ ማር የማቅረብ አቅምን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፣ በአሣ ሀብት ልማትም አርሶ አደሩ በስፋት እንዲሳተፍ 2 ሺህ 56 ሰው ሰራሽ ኩሬዎች ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል።


 

በክልሉ የሸበዲኖ ወረዳ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አሸናፊ ላላሞ፤ በወረዳው የሌማት ትሩፋት መርሀግብር በአምስት ፓኬጆች እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህም አርሶ አደሩ በመንደር ተደራጅቶ በሚያከናውነው ተግባር የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ ምርት አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ገቢውን እያሳደገ ይገኛል ብለዋል። 


 

በወረዳው ሞሮቾና ጋሻ ቀበሌ ካዮ የስጋ ዶሮ እርባታ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አዮብ አላከ እና ጓደኞቹ፤ በተፈጠረላቸውን የሥራ ዕድል 550 ጫጩቶችን ተረክበው በቅርቡ ወደሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ከቀጣዮቹ ሦስት ወራት በኋላ ዶሮዎቹ ለሽያጭ እንደሚደርሱ ገልጸው፣ ከሽያጩ በሚያገኙት ገቢም ሥራቸውን የማስፋፋት ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

ካላቸው 17 የሽግግር ቀፎዎች በዓመት ሦስት ጊዜ ማር እንደሚቆርጡ የገለጹት ደግሞ በንብ መንደር የተደራጁት አርሶ አደር ማሙሌ ባንሶ ናቸው፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረውን ቀፎ ወደ ዘመናዊ ከመቀየር ጀምሮ የማር ምርታቸውና ተጠቃሚነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም