የሀገርን ሉዓላዊነት በህይወት መስዋዕትነት እያስከበረ ላለው ሠራዊታችን ያለን ድጋፍ የማይናወጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ሉዓላዊነት በህይወት መስዋዕትነት እያስከበረ ላለው ሠራዊታችን ያለን ድጋፍ የማይናወጥ ነው
ባህርዳር ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ የሀገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን በህይወት መስዋዕትነት እያስከበረ ላለው ሠራዊታችን ያለን ድጋፍ የማይናወጥ ነው ሲሉ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የሀገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን በህይወት መስዋዕትነት እያስከበረ ላለው ሠራዊታችን ያለን ድጋፍ የማይናወጥ በመሆኑ ከጎኑ በመሰለፍ የደጀንነት ሚናችንን ከምንጊዜውም በተሻለ መልኩ እንወጣለን ብለዋል።
የቀድሞ የሠራዊት አባልና የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ጸጋዬ መኮነን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አብዛኛውን ዕድሜያቸውን የኖሩት በውትድርና የሀገራቸውን ዳር ድንበር በማስከበር ነው።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሚከፍለው መስዋዕትነት የውጭ ጠላትን አሳፍሮ በመመለስ ዳር ድንበሩን በጀግንነት አስጠብቆ እንደሚኖር ተናግረዋል።
መከላከያን ደግፌ ዛሬ በሰልፉ ላይ የተገኘሁት ለእኔ ሰላም እሱ እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት ለመዘከር ነው ብለዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችውን የባሕር በር በሰላማዊ መንገድ ለማስመለስ እየተደረገ ላለው ጥረትም ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ የክቤ የኋላ እንዳሉት፣ ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በማስከበር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ውድ ሕይወቱን እየከፈለ የሚገኝ ሠራዊት ነው።
የቀደሙ አባቶቻችን በአድዋ ተራሮች ጠላት ኢትዮጵያን ለመውረር አሰፍስፎ በመጣበት ወቅት በጀግንነት በመደምሰስ በዓለም ዘንድ ዝናችን ከፍ እንዲል አድርገዋል ብለዋል።
የአሁኑ ሠራዊትም የጽንፈኞችንና የውጭ ጠላቶችን ሴራ በማክሸፍ የአድዋን ድል እየደገመ በመሆኑ፣ የደጀንነት ሚናቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
"የሀገር መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ ማለት የሀገርን አንድነት አስጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ማለት ነው" ያሉት ደግሞ የቀድሞ የሠራዊት አባል ወታደር ማሩ እና ወጣት ሰሎሞን ታደሰ ናቸው።
ወደ ቀይ ባሕር ለመመለስ የተጀመረውን የዲፕሎማሲ አካሄድ እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።
በሰልፉ ላይም የመንግሥት ሠራተኞች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።