የሁሉ መገኛ - ኢዜአ አማርኛ
የሁሉ መገኛ
ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ የሁሉ መገኛ
የገዘፈ ታሪክ፣ የበዙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በአየር ንብረቷ ምቾት ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ አገራት ቱሪስቶች ለመኖር የምትመረጥ ውብ ሀገር መሆኗን ይመሰክራሉ። በኢትዮጵያ የታሪክ ስንቆች፣ የባህል እሴቶች፣ የተፈጥሮ መስህብ ሃብቶችና ሌሎችም አስደናቂ ትውፊቶች ይገኛሉ።
ከዓለም የምትለይባቸውም በርካታ መገለጫዎችም አሏት። የሰው ዘር እና የቡና መገኛ፤ በዓለም ላይ ብቸኛዋ የ13 ወራት ባለቤት፤ ከዳሉል እስከ ራስ ዳሽን የሚዘልቅ የአስደናቂ መልክአ ምድር ባለቤትም ነች። በተፈጥሮ ውበቷ፣ ዘመናትን በተሻገረ ታሪኳ፣ በሕዝቦቿ ባህልና ወግ፣ የቀኝ ገዥዎችን እብሪት እምቢ አልቀበልም በማለት በነፃነት ትግሏ እና በአሸናፊነቷ የምትወሳ ሀገር መሆኗም ይታወቃል።
በአፋር የተገኙ ጥንታዊ የሰው ዘር ቅሪተ አካላትና የድንጋይ መሣሪያዎች፣ የሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ጉዞን ለመረዳት ያስቻለ ነው። በአፋር ምድር ሀዳር አካባቢ የተገኘችው የሉሲ ቅሪተ አካል በዓለም ላይ የሰው ዘር ታሪክን ለማጥናት አስችሏል። ይህም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የሳይንስ ማስረጃዎችን የያዘች ሀገር መሆኗን የሚያመላክት ነው።
የጥንታዊ ሥልጣኔ ማዕከል ሆና በንግድ፣ በአስተዳደር፣ በሥነ ሕንፃና በስነ ጽሁፍ ያላት እምቅ ሃብትና ጥልቅ ታሪክም ይጠቀሳል። በላሊበላ ከድንጋይ የተፈለፈሉ አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር ታሪካዊ ቅርሶች፣ የሐረር ጥንታዊ ከተማነት፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የኦሞ ሸለቆ፣ የሰሜንና የባሌ ተራሮች የሀገር ሀብቶችና መለያ ምልክቶችም ናቸው።
የአባይ ወንዝም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ መገለጫ ከመሆን ባለፈ ለቀጣናዊ የኃይል ትስስር መሰረት ያኖረ ታላቅ ግድብ የተገነባበት ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል እያመነጨ፣ የንጋት ሰው ሰራሽ ሃይቅም ዓሳ እየተመረተበትና የመዝናኛ ስፍራ ሆኗ ተዘጋጅቷል። በመሆኑም ኢትዮጵያ አባይን እና ሌሎችንም በማልማት ከሃይል ምንጭነት ባለፍ የምግብ ዋስትና መሰረት የማድረግ ጥረቷ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ በተለያየ የመሬት ከፍታና በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ ምክንያት በአየር ንብረቷ የታደለች ሀገር ናት። በከፍተኛ ደጋማ አካባቢዎች ቀዝቃዛ ወይም መጠነኛ የአየር ንብረት ሲኖራት በቆላማና በዝቅተኛ አካባቢዎች ደግሞ ሞቃታማና ደረቅ የአየር ንብረት አላት። በዚህም በአንድ ሀገር የተለያዩ ዓለማት የሚገኙባት ድንቅ ሀገር መሆኗን በርካቶች ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ መልክአ ምድርና የአየር ንብረት ለተለያዩ የግብርና ምርቶች፣ ለቡና፣ ለጥራጥሬ፣ ለፍራፍሬ፣ ለእንስሳት እርባታና ለሌሎችም የኢኮኖሚ ዘርፎች ምቹና ተመራጭ ነው። የተዘራ ፍሬ ሁሉ የሚበቅልባት በመሆኗም ለኢንቨስትመንት በቀዳሚነት የምትመረጥ ሀገር ያደርጋታል።
ከኢትዮጵያ ታላላቅ መገለጫዎች መካከል የአድዋ ድል በታሪክ ውስጥ የተለየ ቦታ አለው። በ1888 ዓ.ም የተካሄደው የኢትዮጵያውያን ድል፣ በአፍሪካ ታሪክ የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል አሸናፊ የሆነችበትና የጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ታሪክ የተመዘገበበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑ ይታወቃል። የአድዋ ድል ለአፍሪካውያንና ለዓለም ሕዝቦች የነፃነት ተስፋን ያጠናከረ፣ የጥቁር ሕዝቦችን ክብርና ችሎታ ያሳየ ታሪካዊ ድልም ነው። ዛሬም አድዋ ለኢትዮጵያውያን እና ለመላ አፍሪካዊያን የኩራት ምንጭ ሆኖ በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዓመት 13 ወራት አሉት፤ 12ቱ ወራት እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ሲኖሯቸው፣ 13ኛው ወር ጳጉሜን አምስት ወይንም ስድስት ቀናት ይኖራታል። የ13 ወራት የዘመን አቆጣጠር የቁጥር ልዩነት ብቻ ሳይሆን፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የማንነትና የጥበብ መገለጫዋ ጭምር ሲሆን ኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የምትቀበለውም መስከረም 1 መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የዘመን አቆጣጠሩ በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል እንዲሁም በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የራሱ የሆነ ልዩ ስፍራ አለው።
ኢትዮጵያ የሰው ዘርና የቡና መገኛ በመሆን በዓለም የታሪክ መዝገብ ላይ ልዩ ሰፍራ ይሰጣታል። በባህላዊ ምግቦች፣ የባህል አልባሳት፣ የሙዚቃ ቅኝቶች፣ የበዓላት አከባበር፣ የገዳ ስርአት፣ የሰርግና የሽምግልና ስርአቷ ጭምር ልዩ ያደርጓታል። በመሆኑም የቋንቋና የባህል ብዝሃነቱ በትክክል ሲከበርና ሲጠበቅ፣ የሀገሪቱ የፈጠራ አቅም፣ የማኅበራዊ ግንኙነትና የጋራ እድገት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል ማለት ነው።
ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ጥንታዊ ታሪክ አሻራዎችን የያዘች፣ በተራሮቿና በወንዞቿ የተዋበች፣ በአየር ንብረት ብዝሃነቷ የበለፀገች፣ በአድዋ ድል የነፃነት ኩራቷን ያረጋገጠች ድንቅ ሀገር ነች። የቡና አፈላል ባህሏ፣ የሕዝቦቿ ብዝሃነት፣ የጥንታዊ ሥልጣኔ ቅርሶቿና የተፈጥሮ ሀብቷም መለያዎቿ ናቸው። የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክና ልዩ ሀብቶቿ የትናንት ኩራት ብቻ ሳይሆኑ የዛሬ እና የነገ ስንቅ የሚሆኑ እሴቶች ናቸው። በመሆኑም የካበተውን የሀገር ሃብትና የአብሮነት ትርክት በመገንባት የነገን በመሻት መስራት የትውልዱ አደራ ይሆናል። በተደመረ አቅም በማልማት ለሁሉም የምትመች ጠንካራ ሀገር የመገንባት ጥረትም የጋራ አደራና ሃላፊነት ሆኖ ሊቀጥል ይግባል።