ቀጥታ፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስኬት በራስ አቅም ታላላቅ ልማቶችን ከግብ ማድረስ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ያሳካችበት መንገድ በራስ አቅም ታላላቅ ልማቶችን ከግብ ማድረስ እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉ የቀድሞዋ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ (ዶ/ር)  ገለጹ።

አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን በራሷ አቅም እሴት በመፍጠር፣ የምግብ ሉዓላዊነቷን በማረጋገጥ ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅ፤ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች በአንድ ድምፅ መቆም ይኖርባታልም ብለዋል።

ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ(ዶ/ር)፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ  በራስ አቅም ታላላቅ ልማቶችን ከግብ ማድረስ እንደሚቻል የሚያሳይ አስደናቂ ምሳሌ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ኃይሎችን በመጠባበቅ ሳይሆን በራሷ አቅምና በዜጎቿ ተሳትፎ የሕዳሴ ግድብን መገንባቷ፣ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊከተሉት የሚገባ ተሞክሮ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በቅርቡ አዲስ አበባን መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፤ ከተማዋ በፍጥነት እየተለወጠች መሆኗን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ይህም በቂ አቅም፣ ቁርጠኝነትና የለውጥ ፍላጎት ሲኖር ብዙ ማሳካት እንደሚቻል የሚያመለክት መሆኑን አብራርተዋል።

አፍሪካ ለግብርና የሚሆን ሰፊ መሬት፣ የፀሐይ ብርሃን፣ ውሃና የሰው ኃይል ያላት በመሆኑ፣ የምግብ ፍላጎቷን በራሷ ማሟላት እንደምትችል አመልክተዋል። 

ለዚህም የሚያስፈልገው የአስተሳሰብ ለውጥ፣ የጋራ ቁርጠኝነትና የአገራት ትብብር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም