የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እያበረታታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እያበረታታ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን የምርታማነት አቅም በማጎልበት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚያበረታታ እመርታዊ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
የኢትዮጵያ የብዝኅ ዘርፍ ልማት በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት አመርቂ ውጤት ማስገኘት ያስቻሉ የፖሊሲ እርምጃዎች የሚተገበሩበትን ዕድል ፈጥሯል።
የመደመር መንግሥት የኢንዱስትሪ ዘርፍ መዋቅራዊ ስብራትን ለማረቅ የወሰደው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገር አቀፍ ንቅናቄም በርካታ ስኬቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲመለሱ በማድረግ፣ የፋብሪካዎችን የተኪና የወጪ ንግድ የምርታማነት አቅም ማጎልበት ያስቻለ እመርታዊ ውጤት እያስገኘ ይገኛል።
የምጣኔ ሃብት ምሁራን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የምርታማነት አቅም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር የተመዘገበ ተጨባጭ ውጤት ነው።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪ፣ ከተማና መሰረተ ልማት ፖሊሲ፣ ጥናትና ምርምር ማዕከል አስተባባሪና መሪ ተመራማሪ አማረ ማተቡ፤ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ የምርት አቅም እየገነባ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የአምራች ኢንዱስትሪውን መሰረታዊ ችግሮች በመቅረፍ ዘመናዊና የተሰናሰለ የማምረት አቅምን እያጎለበተ መሆኑን ተናግረዋል።
ማሻሻያው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማ ሽግግርን በማሳለጥ፣ የዘርፉን የዕድገት ውጤታማነት እያላቀ የሚገኝ ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አምራቾች ምቹ ምኅዳርን በመፍጠር ለሥራ ዕድልና ለሃብት ፈጠራ ገንቢ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
ይህም የአምራች ኢንዱስትሪን የተኪና ወጪ የምርታማነት አቅም በማጎልበት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነትና ሚዛን የሚያስጠብቅ ዕድል እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የመደመር መንግሥት የፖሊሲና የአሰራር ሥርዓት እርምጃዎች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የአምራቾችን የምርታማነት አቅም በማላቅ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥኑ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፤ ኢንዱስትሪ ተከታታይ ድጋፍና ክትትል የሚፈልግ ዘርፍ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም የኢንዱስትሪ ዘርፍ የማምረት ውስንነቶችን በመቅረፍ በተኪና ወጪ ንግድ የምርት ዓይነቶች ላይ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ፕሮፌሰር ጣሰው ተናግረዋል።
በቀጣይም የውጭ ምንዛሬ ወጪን በመቀነስና ገቢን በማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን በመጨመርና የዋጋ ንረትን በመቀነስ የአምራቹን ዘርፍ ውጤታማነት የበለጠ ማላቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለግል ኢንቨስትመንት ማስፋፋት፣ ለፋይናንስ፣ ለሥራ ባህል ማደግ፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለግብዓትና ለሌሎች ምርታማነትን የሚያሳድጉ መሰረተ ልማቶች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከፍተኛ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት የኢትዮጵያን የአምራች ኢንዱስትሪ የማምረት አቅም የሚያጎለብት ብቁ ሰው ሃይል ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር የመጣውን የምርታማነት አቅም በማጎልበት የዘርፉን ዕድገት የሚያሳልጥ ቀጣይነት ያለው ሥራ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።