ቀጥታ፡

የጣና ፎረም ኢትዮጵያ የቀጣናው ሰላምና ደህንነት መልህቅ መሆኗን የሚያሳይ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦የጣና ፎረም ኢትዮጵያ የቀጣናው ሰላምና ደህንነት መልህቅ  መሆኗን የሚያሳይ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

"በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ ፖለቲካ ለውጥ" በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው 12ኛው የጣና ፎረም በስኬት ተጠናቋል።


 

የኢትዮጵያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጣና ፎረም የአፍሪካ መሪዎች በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት የሚያደርጉበት ስኬታማ መድረክ ነው።

የጣና ፎረም ሰዎች ንግግራቸውን በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ሳያሽሞነሙኑ ሀሳባቸውን እንደ ልባቸው የሚገልጹበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ከሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

በመሆኑም ጣና ፎረም ባለፉት 12 ዓመታት ተገቢ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ ለአፍሪካ ሕብረት የአህጉሪቷን ሰላምና ደህንነት ሪፖርት በማዘጋጀት ገንቢ ሚና መወጣቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናው መልህቅ ናት ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ በቀጣይም ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዓመታት በፊት ለሱዳን ቀውስ የመፍትሔ አማራጭ በማቅረብ ያከናወነችው አስደናቂ የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲሁም ለሶማሊያ ሰላምና ደህንነት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ፎረሙ ኢትዮጵያ ለሰላምና ጸጥታ በምታደርገው ጥረት የቀጣናው መልህቅ ሆና መቀጠሏን በተግባር የሚያረጋግጥና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የውስጥ፣ የቀጣናው፣ የአህጉሪቷና የዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ትኩረት የምትሰጠው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በሚሰጠው ቁርጠኝነት መሰረት የሚያቀርበው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪም ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይት፣ በድርድርና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመፍታት ብዙ ርቀት መጓዙን ገልጸው፤ ለዚህም ከአዋጅ ባሻገር ወደ ተግባራዊ እርምጃ ተሸጋግሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም