ኢትዮጵያ በራስ አቅም ለመልማት የምታደርገው ጥረት ለአፍሪካ ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው - የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ንኮሳዛ ድላሚኒ-ዙማ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በራስ አቅም ለመልማት የምታደርገው ጥረት ለአፍሪካ ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው - የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ንኮሳዛ ድላሚኒ-ዙማ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ለመልማት የምታደርገው ጥረትና በኃይል ዘርፍ የወሰደቻቸው ድፍረት የተሞላባቸው ውሳኔዎች ለአፍሪካ እድገት ትልቅ ተምሳሌት መሆናቸውን የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ንኮሳዛ ድላሚኒ-ዙማ ገለጹ።
እነዚህ እርምጃዎች ሀገሪቱ በራሷ አቅም ለመልማት ያላትን ብቃት በግልጽ ያሳያሉ ብለዋል።
ሶስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ነገ እና ከነገ በስቲያ በሞስኮ ይካሄዳል።
የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ንኮሳዛ ድላሚኒ-ዙማ ከጉባኤው አስቀድሞ ከኢዜአ ጋር በሞስኮ ቆይታ አድርገዋል።
ድላሚኒ-ዙማ፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ የምታበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእ.አ.አ 2012 እስከ 2017 የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ያገለገሉት ድላሚኒ-ዙማ ኢትዮጵያ አፍሪካን በመልካም ተሞክሮ የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባት አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በዜጎቿ አቅም የምትደገፍ፣ የተሳሰረች፣ ሰላማዊና የበለፀገች አፍሪካን የመገንባት ትልቅ ህልም እውን እንዲሆን የመሪነት ሚናዋን መወጣት እንደሚኖርባት ተናግረዋል።
አህጉሪቱ በገዛ አቅሟ ላይ ያላት እምነት አነስተኛ መሆኑ ለአፍሪካ እድገትና ብልጽግና ትልቁ እንቅፋት እንደሆነም ነው የገለጹት።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውጫዊ ድጋፍን የመጠበቅን ባህል በመስበር በራስ አቅም መቆም እንደሚቻል የሚያሳይ ህያው ምስክር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ውጫዊ ድጋፍን ሳይጠብቁ የህዳሴውን ግድብ በገዛ አቅማቸው መገንባታቸው እጅግ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ወደፊት እንዳይራመዱ ያደረጋቸው የውጭ አካላትን እርዳታ እጃቸውን ዘርግተው መጠበቃቸው እንደሆነም አመልክተዋል።
በመሆኑም ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች የኢትዮጵያን በራስ የመተማመን እሳቤ እና የመከወን አቅም እንደ መልካም ተሞክሮ ሊወስዱት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አህጉራዊ ዘላቂ እድገት ሊረጋገጥ የሚችለው በገዛ ሀገራዊና አህጉራዊ አቅም ላይ ሙሉ እምነት ሲኖር ብቻ እንደሆነ አንስተዋል።
ከግዙፍ የልማት መሰረተ ልማቶች ባሻገር ድላሚኒ ዙማ የአዲስ አበባን ፈጣን የከተማ እድገትና ለውጥ ከተወሰዱ ጠንካራ እርምጃዎች ጋር በማስተሳሰር አንስተዋል።
ሰሞኑን አዲስ አበባን መጎብኘታቸውን የጠቀሱት የቀድሞዋ ሊቀመንበር የከተማዋን ፈጣን ለውጥ በግልጽ እንደተመለከቱና ይህም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ሲኖር ምን ያህል ሰፊ ስራ መስራት እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ያሳለፈውን ፈርቀዳጅ ውሳኔንም አድንቀዋል።
ይህ ውሳኔ ሀገሪቱን በዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ኢነርጂ ሽግግር ሂደት ውስጥ በግንባር ቀደምነት የሚያሰልፋት መሆኑን በመጠቆም የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አህጉራዊ ተምሳሌት እንደሆነ ገልጸዋል።