የትግራይ ክልል ታዳጊዎች የተስፋ ጎህ፤ በትምህርት የሚገነባ የነገ ብሩህ አድማስ!! - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል ታዳጊዎች የተስፋ ጎህ፤ በትምህርት የሚገነባ የነገ ብሩህ አድማስ!!
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በዐዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14/2/ለ/ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የኢፌዴሪ መንግሥት የትግራይ ክልልን የሚያጸና ውሳኔ ወስኗል።
በትግራይ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ለመፍታት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት በሕገ ወጡ ሕወሐት ዕንቅፋትነት ሳይሳካ ቀርቷል። ሰላምን ያልፈለገው የሕገ ወጡ ሕወሐት አመራር ለአራተኛ ጊዜ በጀመረው አውዳሚ ጦርነት ለአራተኛ ጊዜ ተሸንፎ ተጠናቋል። የትግራይ ሕዝብ የራቀውን ሰላም እንዲጎናጸፍ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ እንዲረጋገጥ እንዲሁም ላለፉት በርካታ ዓመታት ያላገኛቸውን የልማት ትሩፋቶች ለማጣጣም እንዲችል ከግጭት አዙሪት መውጣት አለበት።
ለዚህ ደግሞ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚገባውን ቦታ አግኝቶ ሰላሙን ማስከበር፣ ትኩረቱን በልማት ላይ ማድረግና ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጸንቶ መኖር አለበት። እነዚህን ሁኔታዎች ባጠረ ጊዜ ለማመቻቸት እንዲቻል የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት ተመሥርቷል።
በዚህም ባለአደራ አስተዳደር ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ትግራይን የሚያስተዳድር ሲሆን፤ ዋና ተግባሩም የክልሉን የሰላምና የመረጋጋት ችግር በፍጥነት በመፍታት የተረጋጋ ሁኔታን መፍጠር፣ የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ በመዘርጋት ሕዝቡ የመደበኛ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር፣ በጦርነት ምክንያት የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በመጠገንና ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ በሀገር ደረጃ የሚታዩ የልማት ትሩፋቶች ትግራይ ውስጥም መስፋፋት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ከተሰጡት ሀላፊነቶች መካከል ናቸው።
በተጨማሪም የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደየቀያቸው መመለስ፣ በክልሉ ውስጥ ተቋርጠው የነበሩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ማድረግ፣ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ተፈጥሮ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ነጻና ግልጽ ምርጫ ተከናውኖ ትግራይ የፌዴሬሽኑ መደበኛ አካል የምትሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ከፌዴራል የመከላከያ፣ የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት እንዲሁም ከትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ከክልል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በማስረከብ ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱና ተሐድሶ እንዲያደርጉ ሁኔታውን ማመቻቸት፣ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር እንደ አዲስ የማዋቀር ኃላፊነት ይኖረዋል።
በሌላ መልኩም ሰላም እንዲጸና፣ የሕዝቡ ሥነ ልቡና እንዲስተካከልና ወደ ልማትና የመልሶ ግንባታ ሥራ ለመግባት የሚያስችለው ዝግጁነት እንዲኖረው ማድረግ፣ የሚዲያ ሥራዎችን የማስተባበር፤ በየደረጃው የሚደረጉ የሕዝብ መድረኮችን የማዘጋጀትና ለቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና አካታች እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
የባለአደራ አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው ሁሉም ተግባራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ የትግራይ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት ማድረግ አለበት። በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ የክልሉን የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች ከማቅረብና ለቀጣይ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር በዘለለ ረዘም ያለ ስትራቴጂያዊ አንድምታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ አይንቀሳቀስም። ተግባሩንም ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እና መመሪያ መሠረት ያከናውናል።
አዲሱ ባለአደራ አስተዳደር በትግራይ ክልል የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚያሳልጡ አገልግሎቶች ተጀምረዋል። ከእነዚህ ማህበራዊ ዘርፎች ውስጥ ትምህርት የነገ ተስፋዎች የሚታነጹበት፣ የእውቀት ብርሃን የሚፈነጥቅበትና የሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ የሚቀረጽበት ወሳኝ መሰረት ነው።
ትምህርት ቤቶች የሕጻናትና ወጣቶች የእውቀት ማዕድ ብቻ ሳይሆኑ የሰላም፣ የመቻቻል፣ የመተማመንና የጋራ ተስፋ መገንቢያዎችም ናቸው። በመሆኑም በግጭትና በቀውስ የተጎዳ የትግራይ ክልል አካባቢ የትምህርት ሂደት እንደገና መጀመሩ ከመደበኛ አገልግሎት መመለስ ባለፈ ለማህበረሰቡ ማገገምና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
በትግራይ ክልል በተፈጠሩ የግጭትና የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የትምህርት ሂደት ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ መቆየቱ በትውልዱ ላይ ከባድ ተጽዕኖ አሳድሮ ቆይቷል። ይህም በርካታ ሀገር ተረካቢ ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲነጠሉ አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ በግጭት ወቅት ህጻናትና ወጣቶች ለስነ-ልቦናዊ፣ ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠዋል። የትምህርት መቋረጥ የአንድ ትውልድን የእውቀት ጉዞ በማዘግየት የቤተሰቦችን ተስፋና የማህበረሰቡን የወደፊት እድገት የሚፈትን ችግር ነበር።
በዚህም በጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም በመቐለ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት እንደገና መጀመሩ ትልቅ ብስራት ነው። ይህ እርምጃ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ፣ የተቋረጠውን የእውቀት ጉዞ እንዲቀጥሉና የወደፊት ህልማቸውን እንደገና የሚቀርጹበትን ዕድል ይፈጥራል። በተለይም ለረጅም ጊዜ የትምህርት እድል ተነፍጓቸው ለቆዩ ህጻናትና ወጣቶች፣ የትምህርት ቤቶች ዳግም መከፈት የተስፋ በር መከፈት ማለት ነው።
የትምህርት ሂደቱ መጀመር ከክፍል ውስጥ ትምህርት መስጠትና መቀበል ብቻ አይገደብም። ተማሪዎች ከጓደኞቻቸው ጋር እንዲገናኙ፣ ከመምህራን እውቀት እንዲቀስሙ፣ በጋራ እንዲማሩና ማህበራዊ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያስችላል። ይህም በግጭት ወቅት ሊደርስ የሚችለውን የስነ-ልቦና ጉዳት ለመቀነስና ህጻናት የተረጋጋ የዕለት ተዕለት ህይወት እንዲኖራቸው ለመደገፍ ያግዛል።
በተመሳሳይ የትምህርት ቤቶች መከፈት ለወላጆችም ተስፋን ያጭራል። ልጆቻቸው በደህና ተምረው እውቀት እንዲቀስሙ፣ ለወደፊት ህይወታቸው እንዲዘጋጁና የሀገር ተረካቢ ዜጎች እንዲሆኑ ያላቸውን ተስፋ ያድሳል። ትምህርት በትውልድ መካከል የሚተላለፈውን እውቀት ከማጠናከር ባለፈ፣ ለማህበረሰብ እድገት፣ ለስራ ፈጠራና ለዘላቂ ልማት መሰረት ይጥላል።
በክልሉ የማህበራዊ አገልግሎቶች ዳግም መጀመርም የማገገም ሂደቱን የሚያግዝ ወሳኝ እርምጃ ነው። የአየር መንገድ፣ የቴሌኮምና የባንክ አገልግሎቶች መመለስ፣ እንዲሁም የእርዳታ አቅርቦቶች ወደ ክልሉ መጓጓዝ መጀመራቸው የህዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማሻሻልና መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ለማስቀጠል አስፈላጊ ናቸው። ትምህርት ቤቶች ወደ ስራ መመለሳቸውም ከእነዚህ የማገገም ጥረቶች ጋር ተያይዞ የሚታይ አዎንታዊ ለውጥ ነው።
ሆኖም የትምህርት ሂደት መጀመሩ ብቻ የችግሮቹ ሁሉ መፍትሄ አይደለም። በግጭት የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መጠገን፣ የትምህርት ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ መምህራንን መደገፍ፣ በትምህርት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ልዩ የማጠናከሪያ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀትና ለተጎዱ ተማሪዎች የስነ-ልቦና ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል። ሁሉም ህጻናት ያለምንም ልዩነት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማስቻልም የሁሉም አካላት ትኩረት ይፈልጋል።
በመቐለ የተጀመረው የመማር ማስተማር ሂደት ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም በተቀናጀ መልኩ እንዲስፋፋ ማድረግ ወሳኝ ነው። ይህ እንዲሳካ የፀጥታ ሁኔታውን ማረጋጋት፣ የትምህርት ተቋማትን አቅም ማጠናከርና በመንግስት፣ በማህበረሰቡና በልማት አጋሮች መካከል ትብብርን ማሳደግ ይጠይቃል. በዚህ መንገድ ተማሪዎች የተቋረጠውን ትምህርታቸውን ለማስቀጠልና የነገ ህልማቸውን እውን ለማድረግ የተሻለ እድል ያገኛሉ።
በመቐለ ከተማ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደት መጀመሩ ለትግራይ ክልል የማገገም፣ የመተማመንና የተስፋ ምልክት ነው። ትምህርት በግጭት የተጎዳውን ትውልድ ወደ ተሻለ ነገ ለማሸጋገር፣ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከርና ለዘላቂ ሰላም መሰረት ለመጣል የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ ነው። በመሆኑም የተጀመረው አዎንታዊ ለውጥ በተግባር እንዲጠናከርና በክልሉ ያሉ ሁሉም ህጻናትና ወጣቶች የመማር እድላቸውን እንዲያገኙ ዘላቂ ጥረት ማድረግ ይገባል። የትግራይ ህጻናት ዛሬ ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ፣ የነገዋን ሀገር የመረከብ ህልማቸውም እንደገና ህይወት ዘርቶበታል።