ቀጥታ፡

የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በኃላፊነት በመጠቀም ለሀገራዊ ልማት የሚኖራቸውን ሚና ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ በአገሪቱ የተገነቡና በግንባታ ላይ የሚገኙ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ በመጠቀም፣ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት የሚኖራቸውን ሁለገብ ሚና ማጠናከር እንደሚገባ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ከሀገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራትና ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።


 

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፣ ስፖርትን እንደ መዝናኛና ውድድር ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሀገራዊ ልማት ስትራቴጂካዊ ዘርፍና የማኅበራዊ ለውጥ መሣሪያ አድርጎ መመልከት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ስፖርት ዜጎችን የሚያቀራርብ፣ የሥራ ባህልን የሚያጎለብት፣ ወጣቶች በአዎንታዊ ተግባራት እንዲሳተፉ የሚያበረታታ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያነቃቃ እንዲሁም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎን የሚያጠናክር አቅም መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህንን ለማሳካት የመንግሥት ጥረት ብቻ በቂ ባለመሆኑ፣ የስፖርት ማኅበራትና በዘርፉ የሚሳተፉ ሌሎች ተቋማት በጋራ ኃላፊነት፣ በተቀናጀ አሠራርና በተጠያቂነት መርህ መሥራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በተጨማሪም የስፖርት ልማት ዘላቂ ውጤት እንዲያመጣ በፖሊሲ፣ በሕግ፣ በተቋማዊ አቅም፣ በሰው ኃይል፣ በመሠረተ ልማትና በውጤታማ አስተዳደር መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የስፖርት ማኅበራት ውድድሮችን ከማዘጋጀት ባለፈ፣ ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት፣ የስፖርት ሥርዓቱን በማጠናከር፣ ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች እኩል የተሳትፎ ዕድል በመፍጠርና የሚገነቡ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በኃላፊነት በመጠቀም ለሀገራዊ ልማት የሚኖራቸውን ሚና ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የስፖርት ዘርፉ ለሀገራዊ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ፣ የስፖርት ማኅበራት በጋራ ራዕይ፣ በተቀናጀ እቅድና በተጨባጭ ውጤት ላይ ተመስርተው መሥራት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም