የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞዛምቢክ ናካላ ከተማ አዲስ በረራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞዛምቢክ ናካላ ከተማ አዲስ በረራ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17 /2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞዛምቢክ ናካላ ከተማ አዲስ በረራ መጀመሩን አስታወቀ።
ዛሬ የተጀመረው አዲስ በረራ ከማፑቶ እና ቤይራ ቀጥሎ ሶስተኛው መዳረሻ መሆኑ ተገልጿል።
በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ፣በኢትዮጵያ የሞዛምቢክ አምባሳደር ኑኖ ቶማስን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ የተቃኘ ትስስር አላቸው።
የኢትዮጵያ የአየር መንገድ ወደ ሞዛምቢክ ናካላ ከተማ በረራ መጀመሩ የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን አንስተዋል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ከጣና ፎረም ጎን ለጎን በጋራ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ ይህም ሀገራቱ በትብብር የሚሰሩባቸውን አድማስ ለማስፋት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሞዛምቢክ አምባሳደር ኑኖ ቶማስ በበኩላቸው፤ የበረራው መጀመር ቱሪዝምን፣ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ያሉንን ባህላዊ ትውፊቶች እና ሀብቶች ለዓለም ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እና በሞዛምቢክ መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የበረራው መጀመር አዎንታዊ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የአየር መንገድ ግሩፕ የኦፕሬሽን ዘርፍ ሀላፊ ረታ መላኩ በረራው በሞዛምቢክ ሶስተኛ መዳረሻ መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ የአፍሪካ ሀገራትን በማስተሳሰር ንግድና ኢንቨስትመንና ቱሪዝም እንዲስፋፋ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው በረራ መጀመር የዚሁ አህጉራዊ ግብ አካል ነው ብለዋል።