ኢትዮጵያ መድን ከመቻል : የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ መድን ከመቻል : የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ኢትዮጵያ መድን ከመቻል በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ኢትዮጵያ መድን በአራት ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ በስድስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያ መድን በሶስተኛ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር ሊያደርግ የነበረው መርሐ ግብር በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወቃል።
በሶስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር አዲስ አዳጊውን ጋሞ ጨንቻን 1 ለ 0 ያሸነፈው መቻል ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ሁለቱ ክለቦች በ2018 ዓ.ም የውድድር ዓመት ያደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በመቻል አሸናፊነት ተጠናቀዋል።
መቻል በጨዋታዎቹ በተመሳሳይ 1 ለ 0 በማሸነፍ ከመድን ጋር ካደረጋቸው ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ ወስዷል።
ባለፈው የውድድር ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት የ36ኛ ሳምንት መርሐ ግብር መቻል በመሐመድ አበራ ጎል ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የዛሬው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል የሚል ግምት አግኝቷል።