የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊና ሰላማዊ ተግባራትን ለማጠናከር ያሳየው ቁርጠኝነት ያስመሰግነዋል - የተባበሩት መንግስታት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊና ሰላማዊ ተግባራትን ለማጠናከር ያሳየው ቁርጠኝነት ያስመሰግነዋል - የተባበሩት መንግስታት
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊና ሰላማዊ ተግባራትን ለማጠናከር ያሳየው ቁርጠኝነት የሚያስመሰግነው ነው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሃፊ ኦዞኒያ ኦጅሎ (ዶ/ር) ገለጹ።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሃፊ ዶክተር ኦዞኒያ ኦጅሎን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም ቀጣናዊ፣ አካባቢያዊና ሃገራዊ ሰላምና መረጋጋትን በማጠናከር ጉዳይ ላይ አፅንኦት ሰጥተው መክረዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ በሚከበርባቸውና በሚጠናከርበት ርእሰ ሁኔታ ላይም መነጋገራቸው ተገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሃፊ ዶክተር ኦዞኒያ ኦጅሎ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት የመንግስታቱ ድርጅት የሚደግፈው ነው።
ለዚህም አላማ ስኬትም የመንግስታቱ ድርጅት ከጎኗ እንደሚቆም ዶክተር ኦዞኒያ ኦጅሎ ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ባደረጉት ውይይት አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ እንዳለበት የተናገሩት የመንግስታቱ ድርጅት ረዳት ዋና ፀሃፊ ኢትዮጵያ ድንበሬ ተጥሶብኛል ብላ ያቀረበችው ጉዳይ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፈታት እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡
ህግና ስርአትን ማረጋገጥ ፣ የዲዲአር ሂደትን መተግበር፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው መመለስና የህዝብ እውቅና ያለው ህገመንግስታዊ የሲቪል አስተዳደርን ወደ ቦታው በመመለስ ሂደት የመንግስታቱ ድርጅት ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆምና መንግስትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ረዳት ዋና ፀሃፊው አረጋግጠዋል፡፡
አሁን የተገኘው ሰላም በኢትዮጵያ የተጀመረውን የማህበራዊና የኢኮኖሚ የለውጥ እመርታ ለማሳደግና በሃገሪቱም የተረጋጋ ሁኔታ ለማምጣት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለውም ዶክተር ኦዞኒያ ኦጅሎ ጠቁመዋል፡፡
ረዳት ዋና ፀሃፊው አያይዘውም የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊና ሰላማዊ ተግባራት እንዲጠናከሩ ቁርጠኛ መሆኑንና እያደረገ ላለው ትብብር ምስጋና አቅርበው ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይህን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።
የመንግስታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ፀሃፊ ከሁለት ሳምንት በፊት አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ አካባቢያዊ ሰላም እንዲጠናከርና በሃገር ውስጥም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲከበር የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ከጎኗ እንደሚቆም ማረጋገጣቸው ይታወሳል።