ወላይታ ድቻ ሀላባ ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት በመርታት የመጀመሪያ ድሉን አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
ወላይታ ድቻ ሀላባ ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት በመርታት የመጀመሪያ ድሉን አስመዘገበ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ ሀላባ ከተማን 6 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ መሳይ ሰለሞን ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።
መሳይ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሀትሪክ የሰራ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል።
ሱሌይማን ሀሚድ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ቶጓዊው ያኦቪ ጆሴፍ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ቤኒናዊው የሀላባ ከተማ ግብ ጠባቂ ራያን ኦቢን በ82ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
በጨዋታው ወላይታ ድቻ ከፍተኛ ብልጫ ወስዷል።
መርሐ ግብሩ በዘንድሮው የውድድር ከፍተኛ የግብ መጠን የተቆጠረበት ጨዋታ ሆኗል።
በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘገበው ወላይታ ድቻ በአምስት ነጥብ ደረጃውን ከ15ኛ ወደ 6ኛ ከፍ አድርጓል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዲስ አዳጊው ሀላባ ከተማ በአምስት ነጥብ ከነበረበት 6ኛ ደረጃ ወደ 9ኛ ዝቅ ብሏል።
በአምስተኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ሀላባ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ይጫወታሉ።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ነገ ኢትዮጵያ መድን እና መቻል በሚያደርጉት ጨዋታ ፍጻሜውን ያገኛል።