በክልሉ የጤና ልማት ስራዎችን አስተማማኝ ዋስትና ወደ ሚሆኑበት ደረጃ ለማሸጋገር የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ -ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጤና ልማት ስራዎችን አስተማማኝ ዋስትና ወደ ሚሆኑበት ደረጃ ለማሸጋገር የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ -ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
ጂንካ፣ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጤና ልማት ስራዎችን ለማህበረሰቡ አስተማማኝ ዋስትና ወደ ሚሆኑበት ደረጃ ለማሸጋገር የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የማጠናከሪያ ንቅናቄ በጂንካ እየተካሄደ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በክልሉ ትኩረት ከተሰጣቸው ማህበራዊ ልማት ዘርፎች አንዱ ጤና ነው።
በዚህም በክልሉ ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ጤናማ ግለሰብ፣ ጤናማ ማህበረሰብ እና ጤናማ ትውልድ መፍጠር ሀገር ማስቀጠል በመሆኑ ትኩረት ያሻዋል ሲሉም አክለዋል።
የጤና ልማት ስራዎችን ለማህበረሰቡ አስተማማኝ ዋስትና ወደሚሆኑበት ደረጃ ማሸጋገር ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ረገድ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
ለዚህም የጤና ተቋማት ተጨባጭ ውጤት ማምጣት አለባቸው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደሳለኝ በበኩላቸው በክልሉ ህብረተሰቡን ያሳተፈ፣ ጥራቱን የጠበቀ ቀጣይነት ያለው ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዜጎች በፍትሐዊነት የጤና አገልግሎት ተደራሽ ከሚሆንባቸው የጤና ፕሮግራሞች አንዱ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን መሆኑን አመላክተዋል ።
በክልሉ በ2018 በጀት አመት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ5 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አስታውሰው በተያዘው በጀት አመት ተጨማሪ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል ።
ፕሮግራሙን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግም ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት የሚያቀርቡ 87 የማህበረሰብ ሞዴል መድኃኒት ቤቶችን በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃት ተችሏል ብለዋል ።
ተገልጋዮች በጤና ተቋማት እንግልት እንዳይገጥማቸው የህክምና መረጃዎቻቸውን ዲጂታል በማድረግ በፍጥነትና በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል ።
በምክክር መድረኩ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።