ቀጥታ፡

የየም የባህላዊ መድሃኒት እጽዋት ለቀማ ስነ ስርአት ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል

ሳጃ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፡-የየም ሀገር በቀል እሴት የሆነው የባህላዊ መድሃኒት እጽዋት ለቀማ  ስነስርዓት ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውል እንደሚደረግ ተመለከተ።

የየም ባህላዊ የመድሃኒት እጽዋት ለቀማ ''ሳሞ ኤታ'' የተመለከተ ባዛርና የጥናት ሲምፖዝየም በሳጃ ከተማ ተካሄዷል።


 

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል እሴቶችና ሀገር በቀል እውቀት ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ እስከዳር ግሩም በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የየም የመድሃኒት እጽዋት ለቀማ ስነስርዓት በትውልድ ቅብብሎሽ እየተላለፈ የመጣ የማህበረሰቡ ሀገር በቀል እውቀት መገለጫ እሴት  ነው፡፡

ሁነቱም አብሮነት ጎልቶ የሚታይበት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታነት ያለው የወል ሃብት በመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ አስችሎታል ብለዋል።

እሴቱ ባህላዊ ህክምናን በማጎልበትና በምርምር በመደገፍ ለዜጎች ጤና አማራጭ መፍትሄ እንዲሆን እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የመድሃኒት እጽዋት ለቀማ ስነ ስርዓቱንም የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚከናወኑ አመላክተዋል።

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ሞገስ ባልቻ በክልሉ የባህላዊ መድሃኒት ህክምናን ጨምሮ በርካታ ሀገር በቀል እውቀት መኖሩን አንስተዋል፡፡


 

ይህንን አልምቶ እና አዘምኖ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የቆየው እሴቱን ይበልጥ በምርምር ማስደገፍ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይሁን አሰፋ በበኩላቸው፤ ይኽው የየም የባህላዊ ህክምና እውቀት የመድሀኒት እጽዋት የአሰባሰብና አጠቃቀም ስርዓት ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።


 

በየአመቱ ጥቅምት 17 ቦር ተራራ ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተገኘበት ለሰውና ለእንስሳት ጤና መድኃኒትነት የሚጠቅሙ የእጸዋት አይነቶች ይሰበሰባሉ ብለዋል።

ሀገር በቀል እውቀቱን ለማዘመን ትኩረት እንደተሰጠ አንስተው የባህላዊ መድኒቶች በጥናት ተደግፈው የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የሚያስችሉ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

የባህል ህክምና ባህላዊ መድሃኒት ላይ የሚሰሩ የምርምር ስራዎችን ለማጎልበት እየተሰራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለፁት ደግሞ በሐርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶክተር ሙሉጌታ ጉታ ናቸው ።

ባህላዊ የመድሃኒት እጽዋት ለቀማ ስነስርአቱ በየዓመቱ ጥቅምት 17 ላይ መደረጉ ከእለቱ ጋር የሚያያዝ ባህላዊ ምክንያት ያለው መሆኑን አንስተው ይህንንም ነባር እውቀት ለትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራን ነው ብለዋል።

በሲምፖዝየሙ ላይ ከፌደራል፣ ከክልልና ዞን በየደረጃው ያሉ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ መድሃኒት አዋቂዎች ፣የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም