የክልሉ መንግሥት የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን - የአሪ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ መንግሥት የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን - የአሪ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች ነዋሪዎች
ጂንካ፣ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፡-የክልሉ መንግሥት የልማት ውጥኖች የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያሳደጉ በመሆናቸው ለውጤታማነታቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ የአሪ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች ነዋሪዎች ገለጹ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከአሪ እና ከደቡብ ኦሞ ዞኖች ከተወጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር መክረዋል።
ነዋሪዎቹ በዚህ ወቅት እንዳሉት በመደመር መንግሥት በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ አንፀባራቂና አስደማሚ ለውጦች ተመዝግበዋል።
በተለይ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ልማት ከማጠናከር አኳያ ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ዓለምፀሐይ ሻሆ የተባሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪ ጂንካን ጨምሮ በአሪ ዞን ፈጣን እድገት እየታየ መሆኑን ጠቁመው፣ ህዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።
በጂንካ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት እና ግንባታው የተጓተተው የአስፋልት መንገድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም በመደመር መንግስት የተያዙ የልማት ግቦች ሀገሪቱን ወደ ከፍታ የሚያሻግሩ በመሆናቸው ውጥኖቹ እንዲሳኩ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
በደቡብ ኦሞ ዞን የበናፀማይ ወረዳ ነዋሪ አርብቶ አደር ድንቁ ደርታ በበኩላቸው እንዳሉት የመደመር መንግሥት በልማት ወደኋላ ለቀሩ አካባቢዎች ጭምር የመልማት ዕድል የሰጠ ነው።
በዚህም አርብቶ አደሩ ከጠባቂነት ወጥቶ በልማት ጎዳና ላይ ይገኛል ያሉት ነዋሪው፣ ይህም መንግሥት ለአርብቶ አደሩ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል።
ቀደም ሲል በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች ከልማት ይልቅ ግጭት ጎልቶ ይታይ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ከግጭት ይልቅ ልማት የአካባቢው ቀዳሚ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ ችግሮችን በመነጋገር የመፍታት ባህልን ማዳበር የዴሞክራሲ ልምምድን ከማሳደግ ባለፈ የስልጣኔ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
በአሪ እና በደቡብ ኦሞ ዞኖችም አብሮነትን የሚያጠናክሩና ግጭትን የሚያስቀሩ በርካታ እሴቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን እሴቶች በመጠቀም ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።
በተለይም ለግጭት መነሻ የሚሆኑ የኢኮኖሚና ሌሎች ማኅበራዊ ጥያቄዎችን ለይቶ በዘላቂነት ለመፍታት ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የክልሉ የልማትና የሰላም ግንባታ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑም ህዝቡ ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅንጅት እንዲሰራም ጠይቀዋል።
የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ፣ በመካከለኛ እንዲሁም በረዥም ጊዜ ከፋፍሎ ለመመለስ እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው የህዝብን የልማት ጥያቄዎች በጥናትና በተደራጀ አግባብ ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።