ቀጥታ፡

በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የህዝቡ ሁለንተናዊ ትብብር ሊጠናከር ይገባል

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 16 /2019 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የህዝቡ ሁለንተናዊ ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

ከክልሉ የተወከሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የሰላም የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድሯ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ የሕዝቡን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሰላም ለዘላቂ ልማትና ዕድገት ዋነኛ መሠረት መሆኑን ጠቁመው የክልሉ ሕዝብ ሰላምን ለማጽናት ለሚደረገው ጥረት መሳካት ሁለንተናዊ ትብብሩን ሊያጠናክር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም በክልሉ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አብሮነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግሥት አሰባሳቢ ትርክቶችን በማጉላት የሕዝቡን ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለማጠናከር በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንዲሁም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የውይይት መድረኩ ዓላማም ሕዝቡ ለዘመናት የገነባውን በመቻቻልና በፍቅር አብሮ የመኖር እሴቱን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት በክልሉ አሁን ላይ ያለውን ሰላም በማጽናት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች እውን ለማድረግ የሕዝቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ የሚቻለው የሕዝቡ ድጋፍና ትብብር ሲጠናከር መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም